የጅምር ስራ ሃሳቦችን ማበረታታት የሀገርን እምቅ ኃይል ለመጠቀም እንደሚረዳ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ገለጹ።
በሳይንስ ሙዚየም በተከፈተው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ ከተለያዩ ዘርፎች በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ፣የመጀመሪያ ደረጃን የተሻገሩ እና ወደ ገበያ የተቀላቀሉ የስራ ፈጠራ ሃሳቦች ለዕይታ ቀርበዋል።
"ሀገራችን ያሏትን በርካታ ሃብቶች ለመጠቀም ለጅምር ስራ ሃሳቦች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው" ሲሉ ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል።
የሰው ኃይል ልማት ላይ መስራት ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ይህም ለኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ያለው አስተዋፆ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የጅምር ስራ ሃሳቦች የሀገርን እምቅ አቅም ከማውጣት ጎን ለጎን ወጣቱ ያለውን የስራ ፈጠራ ችሎታ እና ኃይል በመጠቀም የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
የተለያዩ ሃሳቦች እና ልምዶች ልውውጥ የሚደረግበት ይህ አውደ ርዕይ፤የስራ ፈጣሪዎችን እና ጀማሪዎችን ከኢንቨስተሮች ጋር ለማገናኘት ያለው እድል ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
የጅምር ስራ ሃሳብ ሀገርን ከተለያዩ ወጪዎች ሊታደጉ የሚችሉ ፈጠራዎች ያሉበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣የመንግስትን ቁርጠኝነትን በማጠናከር እና ተግዳሮቶችን በመንቀስ ረገድ ያሉ ሃሳቦችን በመምረጥ ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚቻልም ነው ሚኒስትሯ የገለፁት።