የዓለም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን ዛሬ ይከበራል፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አጀማመርን እና ፍትሃዊነትን ለማስፈን ያላቸውን ሚና እንመለከታለን፡፡
እ.አ.አ በ1844 በሰሜን እንግሊዝ በሚገኘው የጥጥ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ 28 የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የመጀመሪያውን ዘመናዊ የኅበረት ሥራ አቋቋሙ። ዓላማቸውም ለማኅበረሰቡ ንጹህ፣ ርካሽ እና አማራጭ ያለው ምርት ማቅረብ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ የትብብር እንቅስቃሴው በመላው ዓለም እየተስፋፋ እና ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች እያካተተ ቀጠለ።
ዓለም አቀፉ የኅበረት ሥራ ማኅበራት በእንግሊዝ ተመስርቶ 1ኛው የትብብር ጉባዔውን እ.አ.አ ነሐሴ 19 ቀን 1895 በለንደን አካሄደ።
ከአርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሆላንድ፣ ሕንድ፣ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድ፣ ከሰርቢያ እና አሜሪካ የመጡ ልዑካን በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም መረጃ ለመለዋወጥ፣ የትብብር መርሆዎችን ለማሳደግ እና ዓለም አቀፍ የንግድ ትብብር ለማሳደግ የሚያስችል የኅበረት ሥራ ማኅበራት ትብብር መድረክ ፈጥረዋል።
ዓለም አቀፍ የኅበረት ሥራ ቀን(ICA) ለመጀመሪያ ጊዜ መከበር የጀመረው በ1923 ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ሕጋዊ እውቅና ያገኘው በ1995 ነው፡፡ ዕለቱ ላለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት በየዓመቱ የፈንጆቹ ሐምሌ በገባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ይከበራል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን “የኅበረት ሥራ ማኀበራት-የተሻለ ዓለም ለመፍጠር አካታች፣ ምሉዕ እና ዘላቂ መፍትሔዎች ናቸው" በሚል ጭብጥ ለ103ኛ ጊዜ ዛሬ ይከበራል፡፡
የዘንድሮው የኅበረት ሥራ ማኅበራት ቀን ሲከበር የኅበረት ሥራ ማኀበራት ፍትሐዊ እና ጠንካራ ማኅበረሰብን በመፍጠር ረገድ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና ማጉላትን ታሳቢ አድርጎ ነው።
የዚህ ዓመት ጭብጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈታኝ ሁኔታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን በብዙ መልኩ ይናገራል። ትርፍን ሳይሆን ሰውን የሚያስቀድሙት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጠንካራ ማኅበረሰብን እንዴት መገንባት እንደሚቻል ማሳያዎች ናቸው።
የኅበረት ሥራ ማኅበራት ከጤና እና ከመኖሪያ ቤት እስከ ግብርና፣ ፋይናንስ እና ንፁህ የኃይል ምንጭን በማቅረብ ለማኅበረሰብ ዘላቂነት ያላቸው እና እውነተኛ መፍትሔዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን ከሁለት ዐበይት ዓለም አቀፍ ክንውኖች ጋር ይገናኛል። እነዚህ ቁልፍ ክንውኖች የዘላቂ ልማት ግቦችን በመገምገም ላይ የሚገኘው የተመድ ከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ፎረም እና ሁለተኛው የማኅበረሰብ ዕድገት የዓለም ጉባዔ ናቸው።
እነዚህ ወሳኝ ክንውኖች የኅበረት ሥራ ማኅበራት የአካባቢ መፍትሔ ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፍ የመፍትሔ አካል እንደሆኑ ያስታውሱናል።
ከ12 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በዓለም ላይ ካሉ 3 ሚልዮን የኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል የአንዱ አባል ነው።
300 ትላልቅ የኅበረት ሥራ ማኅበራት ለማኅበረሰብ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እና መሠረተ ልማትን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የገንዘብ ዝውውራቸውም 2,409.41 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የኀብረት ሥራ ማኅበራት ለዘላቂ እና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም ጥራት ላለው የሥራ ዕድል ዋስትና ናቸው፡፡
ማኅበራቱ በዓለም ዙሪያ ለ280 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፣ ይህም ተቀጣሪ ከሆነው የዓለም ሕዝብ መካከል 10 በመቶው ያክል እንደሆነ የተመድ መረጃ ያመላክታል።
የዚህ ዓመት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን ዓላማዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዘላቂ እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጉላት፣ የማኅበራቱን የሥራ ፈጠራ እና ምሥረታ ሥነ ምህዳር ማጠናከር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠናከሩባቸውን ሕጎች እና ፖሊሲዎችን በማበረታታት እንዲሁም የኅበረት ሥራ ማኅበራትን ዓላማ የተረዳ አመራርን ማሳደግ እና ወጣቶችን በንቅናቄው ማሳተፍ ናቸው።
ኅብረት ሥራ በኢትዮጵያ
ኅብረት ሥራ በኢትዮጵያ በዕድር፣ እቁብ፣ ደቦ እና በመሳሰሉት ባህላዊ መንገዶች የሚታወቅ ሲሆን፣ ዘመናዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴ ከተጀመረ 6 አሥርት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ከኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን በማረጋጋት ረገድ እየተጨዋቱ ያሉት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት ከልማት አጋሮች እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲጠናከሩ እየሠራ ይገኛል፡፡
የማኅበራቱ ተጠናክሮ መቀጠል ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ቁልፍ መሣሪያ ሆነው ይገኛሉ።
በዓለም ለ103ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን በኢትዮጵያ የሚከበረው ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ