ከነዳጅ ዘይት እና ጋዝ አምራች ኩባንያዎች የሚያፈተልከውን አደገኛ ‘የሚቴን ጋዝ’ ለመጠቆም የተሰራችው 88 ሚሊዮን ዶላር የወጣባት 'ሜቴን-ሳት' የተባለች ሳተላይት መጥፋቷ ተዘገበ።
ባለፈው ዓመት በስፔስ ኤክስ ፋልከን 9 መንኮራኩር ወደ ጠፈር መጥቃ የነበረችው ሳተላይት፤ ከ14 ወራት አገልግሎት በኋላ ነው መጥፋቷ የታወቀው።
የምድርን አንድ ሶስተኛ ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነውን ሜቴን የተባለ አደገኛ ጋዝ ብክለት ለመቀነስ በአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች፣ በጎግል ኩባንያ እና ጄፍ ቤዞስ የገንዘብ ድጋፍ ተሰርታ ባሳለፍነው 2024 ነበር ወደ ጠፈር የመጠቀችው።
'ሜቴን-ሳት'፥ የነዳጅ ቁፋሮ ቦታዎችን የማስተላለፊያ መስመሮች እና ጋዝ ማምረቻዎችን ከጠፈር ላይ ሆና በማሰስ፤ ይህ አደገኛ ጋዝ ያፈተለከበትን ቦታ በመለየትና ትክክለኛ ቦታውን በመጠቆም በቦታው ማስተካከያ እንዲደረግ የምታግዝ ነበረች።
ወደጠፈር ከመጠቀችበት ጊዜ ጀምሮ በየ95 ደቂቃ ያለማቋረጥ ምድርን በመዞር በየዕለቱ መረጃ ስትልክ የቆየች ሲሆን፤ ከባለፉት አስር ቀናት ወዲህ ግን ከምድር ጋር ያላት ግንኙነት ተቋርጦ መጥፋቷ ታውቋል።
ምድርን በቀን ለ15 ጊዜያት እየዞረች ከምድር 50 ሜትር ከፍታ ላይ ያፈተለከ ሜቴን ጋዝን እንድትለይ ተደርጋ የተሰራችው ሜቴን-ሳት ቢያንስ ለአምስት ዓመታት እንድታገለግል የተሰራች እንደነበረች የሮይተርስ ዘገባ ያመላክታል።