ትረፊ ያላት የስደተኛዋ ነብስ

12 Days Ago 148
ትረፊ ያላት የስደተኛዋ ነብስ

የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እና ቤተሰብን እያመሰቃቀለ ያለው ሕገ-ወጥ ስደት የብዙዎች ስጋት እንደሆነ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል።

ለዚህ የሚዳርጉ ገፊ ምክንያች ላይ ማተኮር በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ስደተኞች እና የሚመለከታቸው አካላት ይናገራሉ።

የአሁኗ ከስደት ተመላሽ ምህረት ረዘነ በጓደኞቿ ግፊት መሰደድን ምርጫ አድርጋ ባህር አቋርጣ ወደ የመን ታቀናለች።

የመን ስትደርስ ደላሎች ተጨማሪ ገንዘብ ካልከፈለች ወደ ሀገሯ እንደሚመልሷት ያስጠነቅቋታል።

ለእናቷ በመደወል ያላቸውን መሬት ሸጠው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲልኩላት ታደርጋለች።

ጀልባው 120 ስደተኞችን ይዞ ጉዞውን ይቀጥላል።

በጉዞው ላይ ብዙ ፈተናዎች እንዳየች ምህረት በተለይ ከኢቲቪ ጋር በነበራት ቆይታ ትናገራለች።

 

እርሷ እንደምትለው፦ ጀልባው የመናወጥ አደጋ አጋጥሞት ባህር ውስጥ ወድቃ በሌላ ስደተኛ አማካኝነት ሕይወቷ ሊተርፍ ችሏል።

ጉዞው የሞት ሽረት ነው የምትለው ከስደት ተመላሿ፤ ስደተኞቹ በሬሳ ላይ እየተረማመዱ ያቋረጧቸው መንገዶች ስለመኖራቸው ታስታውሳለች።

ከኢትዮጵያ እስከ ሳውዲ 4 ደላሎችን ማግኘቷን የጠቀሰችው ምህረት፤ በየሀገሩ ስንደርስ ገንዘብ ይጠይቁን ነበር ብላለች።

ከዛ ሁሉ ስቃይ በኋላ ሳውዲ ስትደርስም ሕልሟ ተጨናግፎ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ መደረጓን ነው የምትናገረው።

"ፈጣሪ በህይወት አትርፎኛል" የምትለው ከስደት ተመላሿ፤ ሁሉም ሰው ከእኛ ሊማር ይገባል፤ ሕገ-ወጥ ስደትም ምርጫ ሊሆን አይገባም ስትል ታስጠነቅቃለች።

ሌላኛዋ ከስደት ተመላሽ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖር የነበረች ታዳጊ ስትሆን፤ ትምህርቷን እስከ 8ኛ ክፍል ተከታትላለች።

ጓደኞቿ ወደ ሳውዲ ማቅናታቸውን ስትሰማ እርሷም ከኩዮቿ ጋር በባህር ወደዚያው በማቅናት ለ5 ወራት ሰራች።

በቆይታዋ የአዕምሮ ጭንቀት እንደያዛት የምትናገረው ከስደት ተመላሿ፤ ረጅም ጊዜ በእስር እና በእንግልት እንዳሳለፈች ትናገራለች።

ስደት ለበርካቶች ለመለወጥ ምክንያት ሊሆንላቸው እንዳልቻለም ትጠቅሳለች።

በፍትህ ሚኒስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጽ/ቤት ቡድን አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ቀለሜ በበኩላቸው፤ 4 መደበኛ ያልሆኑ የሕገ-ወጥ ስደተኞች የጉዞ መስመሮች እንዳሉ ይገልፃሉ።

ሰሜናዊ የጉዞ መስመር፣ በተለምዶ ኩርሙክ የሚባለው የጉዞ መስመር፣ ምስራቃዊ የጉዞ መስመር እና ደቡባዊ የጉዞ መስመርን በመጠቀም ዜጎች በሕገ-ወጥ ስደት እየተንገላቱ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህ ሕገ-ወጥ ጉዞ ስደተኞች በደላሎች ከሚደርስባቸው እንግልት እና ድብደባ ባለፈ በባህር የመስመጥ አደጋ ጭምር እንደሚያጋጥማቸው አንስተዋል።

ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን አግተው ብር አስልኩ ማለትን ጨምሮ የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈፀም የብዙ ቤተሰቦችን ሕይወት እንዳመሰቃቀሉ ይጠቅሳሉ።

ሕገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረት መንግሥት ብዙ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተው፤ ዜጎች በደላሎች ባዶ ተስፋ እንዳይታለሉ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ መጓዝ አንዳለባቸውም በፍትህ ሚኒስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጽ/ቤት ቡድን አስተባባሪው አቶ ኢያሱ ቀለሜ ይመክራሉ።

በሜሮን ንብረት


Feedback
Top