ማይክ ታይሰን ከ19 ዓመታት በኋላ ዛሬ ምሽት በቡጢ ፍልሚያ ይታያል

18 Days Ago 739
ማይክ ታይሰን ከ19 ዓመታት በኋላ ዛሬ ምሽት በቡጢ ፍልሚያ ይታያል
የዓለማችን የምንጊዜም ታላቁ ቦክሰኛ ማይክል ጄራርድ ታይሰን ከ19 ዓመታት በኋላ ዛሬ ምሽት ዳግም በቡጢ ፍልሚያ ይታያል፡፡
 
ታይሰን የቡጢ ፍልሚያውን የሚያደርገው በ31 ዓመት ከሚያንሰው ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ጄክ ፖል ጋር ነው፡፡
 
ማይክ ታይሰን በቦክስ ዓለም ያለውን የቀደመ ገናና ስም ለማስጠበቅ የ27 ዓመቱ ጄክ ፖል ደግሞ አዲስ ታረክ ለመጻፍ ይፋለማሉ፡፡
 
ቴክሳስ ውስጥ በሚገኘው ኤቲ ኤንድ ቲ ስታዲየም የሚደረገውን ይህን ተጠባቂ ፍልሚያ ኔትፍሌክስ በተለያዩ አማራጮች በመላው ዓለም በቀጥታ ያስተላልፈዋል፡፡
 
“አይበገሬው”፣ “ብረቱ ማይክ” እና “አውሬው” የሚሉ ቅጽል ስሞች ያሉት ማይክ ታይሰን ዳግም በፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር መመለሱ አድናቂዎቹን በሁለት ጎራ ከፍሏል፡፡
 
ገሚሶቹ በቦክስ ዓለም የ50 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎች አሸናፊ የሆነውን ማይክ ታይሰንን ዳግም በሪንግ መመልከታቸው ሲያስደስታቸው ገሚሶቹ ደግሞ ቦክሰኛው በጉልምስና ዕድሜው ወደ ቡጢ ፍልሚያ መመለሱ ለጤናው እና ለቀሪ ዕድሜው አስግቷቸዋል፡፡
 
ማይክ ታይሰን እ.አ.አ ከ1985 እስከ 2005 ባደረጋቸው 56 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎች በ50ዎቹ ድል ሲቀዳጅ በ6ቱ ብቻ ሽንፈት ቀምሷል፡፡
ቦክሰኛው ድል ካስመዘገበባቸው ግጥሚያዎች ውስጥ 44ቱን ያሸነፈው በዝረራ ነበር፡፡
 
በተቃራኒው ጄክ ፖል እስካሁን 10 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎችን አድርጎ በ9ኙ ድል ሲቀናው በአንዱ ብቻ ተሸንፏል፡፡
 
ጄክ ፖል ከፕሮፌሽናል የቡጢ ሙያው ባሻገር በተውኔት እና በዩቲዩብ በርካታ ተከታዮች እንዳሉትም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
 
ናርዶስ አዳነ

Feedback
Top