"እንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ" - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

2 Mons Ago 282
"እንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ" - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ስንደቃላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት በዛሬው ዕለት ለ17ኛው ጊዜ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ይከበራል፡፡

ዕለቱን በስንደቅ ዓላማ ፊት ቆመን ስናከብር ያለውን ትርጉምና ክብር በአግባቡ በመረዳት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ዓርማ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት፣ የጥንካሬያችን ሐውልት፣ የድላችን ዓርማ፣ የሉዓላዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የኅብረ ብሔራዊ አብሮነታችን ዋስትና መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ተገብውን ክብርና ፍቅር መስጠት ይገባል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው። ኢትዮጵያውያን በደረሱበት የዓለም ክፍሎች ይዘውት የሚጓዙት ትልቁ ስንቅና ትጥቅ በልባቸው የተሳለው የሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ነው።

ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው ስኬቶችና ድሎች ምሥጢሩ ከሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ጋር የተቆራኘ ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ፣ የአፍሪካ የነጻነት ምልክትም ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ክቡሩንና ዝናዉ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያውን ዛሬም ሆነ ነገ እንደ ትናንቱ መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፡፡ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማው እንዳትደፈርና የሀገሩ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በጦር ሜዳ ዐጥንቱን የሚከሰክሰው፣ ደሙን የሚያፈስሰው ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ነው።

በደምና ዐጥንት ተጠብቆ የቆየውን የሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ ማፅናት የሚቻለው በተሰማራንበት የሥራ መስክ ተግባራችንን በትጋት ስንከውን፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ስንታትር፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮች በሀገር በአርበኝነት ስሜት ስንዋጋ፣ ሰላማችን አፀንተን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ስናረጋግጥ እንዲሁም በኅብር ተናብበን መኖር ስንችል መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም።

በምግብ ራሱን የማይችል ሕዝብና ሀገር ሉዓላዊነቱ በተሟላ ሁኔታ ተረጋግጧል ማለት አይቻልም። ይህ የሚረጋገጠው ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተግቶ ሲሰራ ብቻ ነው። በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን ለማፅናትና የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር ከፍ ለማድረግ በሁሉም መስክ ሃገራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ዳግም ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት።

"ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ”


Feedback
Top