"ጫካን ለአራዊት በመተው ሃሳባችንን በፓርላማ እና በጠረጴዛ ዙሪያ መምከርና መሞገትን መልመድ አለብን" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

6 Mons Ago 1442
"ጫካን ለአራዊት በመተው ሃሳባችንን በፓርላማ እና በጠረጴዛ ዙሪያ መምከርና መሞገትን መልመድ አለብን" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ሀገሪቷን ወደ ቀውስ መንገድ እየገፉ የሚገኙ ምክንያቶች መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ያነሳሉ፡፡

ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ያለው አንዱና ዋነኛ መፍትሄ ንግግር እና ውይይት በማድረግ ያሉ ችግሮችን እና ያለመግባባቶችን መፍታት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሲገለፅ ቆይቷል፡፡

በዚህ ዙሪያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያቶች ሰላም ለማምጣት እና ለመደራደር "መቼም፤ በየትኛውም ቦታ" ዝግጁ ነኝ ሲል ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡

ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ምላሽ ከሰጡባቸው ሃሳቦች አንዱ መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው፤ ጦርነት ለሀገር የሚሰጠውን አስቀያሚ መልክ እና ገፅታ አብራርተዋል፡፡

"ጦርነት መጀመር በጣም ቀላል ነገር ነው፤ ከኪስ ውስጥ በሚወጣ ትንሽ ክብሪት እሳት እንደሚለኮሰው ነው፤ በተለኮሰው መጠን ልክ አይጠፋም፤ ማገዶ አውድሞ፣ ቤት አንድዶ ነው ሚጠፋው፤ እሳት መለኮስና ማጥፋት እኩል አደለም፤ ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የጥይት ድምጽ ይብቃን የምንለው" ሲሉ የጦርነትን አስቀያሚነት ገልፀዋል፡፡

"ጦርነት እንዳይጀመር ያልከፈልነው ዋጋ የለም፤ ለምሳሌ ሸኔ ጋር አባገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ልመና ጫካ ልከናል፤ ከህወሓት ጋር ባለሀብቶችን ልከን የጥይት ድምጽ ትግራይ ላይ አያስፈልግም አስቁሙ ብለናል፤ አማራ ክልል በተመሳሳይ፤ ስንለምን የደከምን ይመስላቸውና ያስቸግራሉ፤ አንገዳደል ሲባል ዝግጁ መሆን ካልቻልን አንዴ ከገባንበት በኋላ ጦርነት ክፉ ነገር ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ጫካን ለአራዊት በመተው ሃሳብን በፓርላማ እና በጠረጴዛ ዙሪያ መምከር እና መሞገትን መልመድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰላም እና እርቅ ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት ጋረደው አሰፋ፤ ይህ ሀሳብ ሀገራችን ከዚህ ቀደም ሞክራው የማታውቀው ችግሮችን በንግግር እና በውይይት መፍታት በሚለው መንገድ እንድትጓዝ የሚያስችላት ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

ሀገራችን በበርካታ ጦርነቶች ውስጥ አልፋ የከፈለችው ዋጋ እልፍ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ዋጋ የማያስከፍል አንዱ ለሰላም መምከር እና መደራደር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን ገልፀው፤ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኋላ የሚጎትተን ጋሬጣ ነው ይላሉ፡፡

አሁን የተሸነፈ የሚመስል በሌላ አጋጣሚ አሸናፊነትን ሲያገኝ ብድር ለመመለስ መሄዱ እንደማይቀር የሚገልፁት ባለሙያው፤ ከዚህ ይልቅ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍኑ ሃሳቦች ብልጫ ቢሰጣቸው መልካም እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

ወደ ሰላም ለመምጣት ዝግጁነትን ተከትሎ የሚመጣው ድርድር ሰጥቶ መቀበልን እንደያዘ ገልፀው፤ ከዛም ባሻገር የተሸናፊነትን ስሜት የሚያርቅ እና ቂም በቀልን የሚያጠፋ ሊፈራ የማይገባው ሃሳብ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡

አክለውም፤ ለአንድ አካል ብቻ የማይተወውን ይህን ሃላፊነት በመወጣት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ ልናወጣት እንችላለን ሲሉ ይናገራሉ፡፡


Feedback
Top