"የኢቢሲ ስጦታ ለ60 ዓመታት 6 ሺህ መጻሕፍት"፡- አንጋፋነትን የሚመጥን ማኅበራዊ ኃላፊነት

5 Mons Ago 1470
"የኢቢሲ ስጦታ ለ60 ዓመታት 6 ሺህ መጻሕፍት"፡- አንጋፋነትን የሚመጥን ማኅበራዊ ኃላፊነት
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “የዕውቀት፣ የጥበብ እና የመረጃ ቤት ነው” ይላሉ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፡፡ ኢቢሲ በሬዲዮ ተወልዶ፣ በቴሌቪዥን ጎልምሶ፣ በኤፍ ኤም ቀድሞ፣ በሳይበር መዲያ ዘምኖ 100 ዓመታትን ሊደፍን ጥቂት የቀረው አንጋፋ ተቋም ነው፡፡
 
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ይዘትን በማሻሻል በበለጠ ጥራት ወደ ህዝብ ለመቅረብ ሪፎርም ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የሥራ ቦታን በማዘመን ዓለም የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን፣ የባለሙያዎቹን አቅም የመገንባት እና ይዘትን የሚያጎለብቱ ማሻሻያዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
 
ኢቢሲ በሚዲያው ዘርፍ የኢትዮጵያ የበኩር እንደመሆኑ የማስተማሩን፣ የማሳወቁን፣ መረጃ የመስጠቱን እና የማዝናናቱን ኃላፊነት እየጠወጣ ሲሆን አንጋፋ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሌሎች ሚዲያዎች መመሥረትም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡
 
እነዚህን የተቋቋመለትን ዓላማዎቹን ከመፈጸም ጎን ለጎንም እንደ ሀገር አስፈላጊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ማኅበራዊ ኃላፊነቶቹን ሲወጣ ቆይቷል፤ እየተወጣም ይገኛል፡፡
 
ይህንን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እያጠናከረ መጥቶ የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 24ኛ የምሥረታ ዓመትን ምክንያት በማድረግ "ለተሻለ ነገ እናንብብ" በሚል መሪ ቃል የመቶ ቀናት የንባብ ዘመቻ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ የንባብ ዘመቻ የፖለቲካ፣ የአካዳሚ፣ የሐይማኖት እና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡
 
ዘመቻው በትውልድ መካከል ያለውን ድልድይ ለማጠናከር የተቻለበት ሆኖ በተሳከ ሁኔታ ተጠናቅቋል፡፡ በዚህም በመሪ ቃሉ ላይ እንደተጠቀሰውም ለኢትዮጵያ መፃዒ ጊዜ የተሻለ ትውልድ የሚፈጠርበትን ማሳያ ሻማ ለኩሷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የ100 ቀናት የንባብ ዘመቻውን ማጠቃለያ ብዙዎች ጎብኝተው መጻሕፍትን የሸመቱበትን የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቶ የበለጠ ሕይወት ሰጥቶታል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ100 ቀናቱ የንባብ ዘመቻ ማጠናቀቂያ ላይ "መጻሕፍት ቤተኛ" በሚል ባስተላለፉት መልዕክት አሰላሳይ እና በሀሳብ ገበያ የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ንባብ ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ምሥረታ በዓልን አስመልክቶ ያዘጋጀውን የንባብ ዘመቻም አድንቀው፣ ሌሎች ተቋማትም ይህንን አርዓያነት እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡
 
መንግሥት በአብርሆት የጀመረውን የቤተ መጻሕፍት ግንባታ ወደ ክልሎችም ለማስፋት እየሠራ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ መጪው ጊዜ ክረምት በመሆኑም ሕፃናት እና ተማሪዎች ንባብ ላይ የሚያሳልፉበትን ሁኑታ ማመቻቸት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የመቶ ቀናት የንባብ ዘመቻ ማጠቃለያ ላይ ያስተላለፉት ጥሪ ተቀብሎ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
 
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኢንሼትቭ የወሰደው ኮርፖሬሽኑ "የኢቢሲ ስጦታ ለ60 ዓመታት 6 ሺህ መጻሕፍት" የሚል ዘመቻ መጀመሩን በዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ አብስረዋል፡፡
 
አቶ ጌትነት እንዳሉት ይህ በቀጣይ ዓመት የሚከበረውን 60ኛ ዓመት የቴሌቪዥን ምስረታ በማስመልከት የሚካሄደው መጻሕፍትን የማሰባሰብ እንቅስቃሴ አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የማኅበረሰቡን የንባብ ባህል ለማጎልበት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዱ አካል ነው፡፡
 
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዕውቅና ኮርፖሬሽኑ የንባብ ባህልን ለማሳደግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብርታት እንደሚሆነው የገለጹት አቶ ጌትነት፤ የ“መጻሕፍት ቤተኛ” ንቅናቄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
 
 
ሚዲያ “የዕውቀት፣ የጥበብ እና የመረጃ ቤት ነው” ነው የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ኢቢሲ የህዝብ አገልጋይነቱን የበለጠ ለማጉላት “ኢቢሲ ወደ ይዘት” የሚል ንቅናቄ መጀመሩን አውስተው፣ ይዘትን ከማሻሻል ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
 
በዚሁ መሰረትም ኮሮፖሬሽኑም ሕፃናት እና ተማሪዎችን ማዕከላዊ ትኩረት አድርጎ የህብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማጎልበት የሚያግዙ የተለያዩ መጻሕፍትን የማሰባሰብ ለአንባቢያን ተደራሽ የማድረጉን ተግባር ሰኔ 01 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ጀምሯል፡፡
 
ኮርፖሬሽኑ ንቅናቄውን የበለጠ ህዝባዊ ለማድረግም ሠራተኞቹን፣ አድማጭ ተመልካቾቹን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ የሰበሰባቸውን የተለያዩ መጻሕፍት ለጋምቤላ እና ደሴ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት በመስጦታ በማበርከት ጀምሯል፡፡ ይህ ስጦታ ለሁሉም ክልሎች የሚቀጥል ይሆናል፡፡

Feedback
Top