የአሜሪካ "ጎልደን ዶም" ፀረ-ሚሳኤል የኒዩክሌር ጦርነት ቀስቃሽ ነው፦ ሰሜን ኮሪያ

1 Day Ago 1003
የአሜሪካ "ጎልደን ዶም" ፀረ-ሚሳኤል የኒዩክሌር ጦርነት ቀስቃሽ ነው፦ ሰሜን ኮሪያ

አሜሪካን ከቀጣዩ ዘመን የአየር ላይ ጥቃት ይታደጋል የተባለው "ጎልደን ዶም" የተሰኘው ፀረ-ሚሳኤል ተቃውሞ እየተነሳበት ነው። 

ሰሜን ኮሪያ ከሩስያ እና ከቻይና በመቀጠል የሚሳኤል ሥርዓቱ ከባድ አደጋ ይደቅናል በሚል ተቃውማዋለች።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ በይፋ ያስተዋውቁታል ተብሎ የሚጠበቀው "ጎልደን ዶም" አሜሪካ "በቀጣዩ ትውልድ" ሊቃጣባት የሚችል የባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ማንኛውንም የአየር ጥቃት ያከሽፋል ተብሏል።

የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን የትራምፕን የሚሳኤል ጋሻ እቅድ "የአሜሪካ ሁሉን አውቃለሁ ባይነት ከፍታ እና ትዕቢተኝነት" ማሳያ ነው ብሏል።

የ"ጎልደን ዶም" ፀረ-ሚሳኤል ሥርዓት የታችኛውን የጠፈር ክፍል የጦር ቀጣና ያደርጋል፤ አለማቀፍ የኒዩክሌር ፉክክርን ይፈጥራል ሲል መቃወሙንም የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ፒዮንግያንግ የዋሽንግተን "ጎልደን ዶም" የሚሳኤል ሥርዓት የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ልማትና ሙከራዋን ክፉኛ እንደሚያደናቅፍ ታምናለች፤ የፀረ-ሚሳኤል ሥርዓቱን ጥሰው የሚያልፉ ሚሳኤሎችን ለማምረትም ልትገደድ ትችላለች።

በአውሮፓውያኑ 2022 የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቀች ሀገር መሆኗን በይፋ ያወጀችው ሰሜን ኮሪያ፤ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ በሚሳኤል ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

በ2025 መጀመሪያ ባለ ሀይፐርሶኒክ አረር ተሸካሚ የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል በማስወንጨፍም ዋሽንግተንን ማስጠንቀቋ የሚታወስ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር እንደ ሰሜን ኮሪያ ካሉ ሀገራት ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለሚመክተው "ጎልደን ዶም" እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት ለመያዝ ማቀዱን ቢቢሲ ዘግቧል።

የግዙፉን የሚሳኤል መቃወሚያ ሥርዓት እቅድ ቻይና እና ሩስያም ነቅፈውታል።

ቤጂንግ ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ፥ የ175 ቢለዮን ዶላር ፕሮጀክቱ "የአንድ ሀገር የደህንነት ማረጋገጫ እርምጃ ሌላ ሀገርን ብሎም ዓለም አቀፉን የኃይል ሚዛን እና መረጋጋት አደጋ ላይ መጣል የለበትም የሚለውን መርህ ይጥሳል" ብላለች።

ሩስያም "ጎልደን ዶም" ውጥረት የሚያባብስ እና የሀገራትን የጦር መሳሪያ ፉክክር የሚያስፋፋ መሆኑን አስታውቃለች።

በፋሲካው ታደሰ


Feedback
Top