የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣትና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በርካታ ኢኮኖሚስቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
ይሁንና የግብዓትና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ዕጥረት፣ ደካማ የኢንዱስትሪዎች ትስስር፣ ዝቅተኛ የሰው ኃይል ምርታማነት፣ የማስፈጸም አቅም ውስንነት እና ከፀጥታ መደፍረስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ችግሮችን በመቅረፍ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት የሚረዱ 29 የኢኮኖሚ ዞኖች መለየታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በሀገር ውስጥ ከ150 በላይ ኢንቨስተሮች እየሰሩባቸው የሚገኙ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገኙ፤ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎችም የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተገልጿል።
ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርት በማምረት ረገድ እያበረከቱ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።
ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ የ1.9 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች መመረታቸውን ለኤፍ ኤም አዲስ የገለጹት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተኪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መሳዬነህ ውብሸት ናቸው።
በዘንድሮው ዓመት ዘጠኝ ወራት ደግሞ በእጅጉ ብልጫ በማሳየት የ3.1 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች መመረታቸውን ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ የተመረቱ ጫማዎችና አልባሳት እንዲሁም የተለያዩ ምርቶች በአውሮፓና በተለያዩ መዳረሻዎች ተፈላጊ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ253 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ኦላኒ፤ በዘንድሮ ዓመት ብቻ 86 የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደሥራ መግባታቸውን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለው የኅህብረተሰቡ ግንዛቤ ማደጉን አመላክተዋል።
በርካታ ዜጎች አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራት ላይ ያለውን ሁኔታ በመረዳት በብዛት እየተጠቀሙ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚጠናከር ጠቁመው፤ በግብዓት፣ በመሰረተ ልማትና በኃይል አቅርቦት እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች አልሚዎችን ለመሳብ የሚደረገው ጥረትም ቀጣይነት እንደሚኖረው አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአምራች ኢንዱስትሪው ልማት አንዱና አስፋላጊ ነገር ኢነርጂ በመሆኑ የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር መናገራቸውም አይዘነጋም።
እያመረተ የሚሄድ ሀገር ችግሮችን እንደሚሻገር አንስተው፤ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በስፋት የመጠቀም ልምድ ሊዳብር እንደሚገባም መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በጌትነት ተስፋማርያም
#EBC #EBCdotstream #Manufacturingindustry