ኢትዮጵያና ጣልያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት በ1880ዎቹ ወቅት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።
በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖዋን ማስፋፋትን ዓላማ ያደረገችው ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር ሁለት ጊዜ ጦርነት ገጥማ መሸነፏም አይዘነጋም።
ከድህረ ኢትዮ-ጣልያን ጦርነቶች በኋላ ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አገም ጠቀም እያለ መዝለቁን የወቅቱ ፖለቲከኞች ሲገልጹት ቆይተዋል።
በኋላም በጥንታዊቷ ሮም ፒያሳ አደባባይ ቆሞ የነበረው ታሪካዊው የአክሱም ሐውልት በ1997 ዓ.ም ወደኢትዮጵያ እንዲመለስ መደረጉ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በር የከፈተ እንደነበር ጉዳዩን ያጤኑ አካላት ያስታውሱታል።
እየተሻሻለ የመጣው የኢትዮ-ጣልያን ግንኙነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ በትምህርት፣ በባሕልና በኢንቨስትመንት ይበልጥ ተጠናክሮ ብቅ ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ጣልያን በልማት እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዘርፎች ላይ የምታደርገውን ድጋፍ ማጎልበቷን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሥድስት ዓመታት በበፊትም የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፍ እንዲል ማስቻሉን የተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ዘግበውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በ2011 እና በ2015 ዓ.ም ወደሮም አቅንተው የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ላቅ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማድረጋቸውን ይታወሳል።
ከዚህ ባለፈ ጣልያን በኮንስትራክሽን፣ በባሕልና ቅርስ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በማሳደግ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በግንባታው ዘርፍ ሰፊ ተሳትፎ ያለው ሳሊኒ ኮንስትራክሽንም የዓባይ ግድብና የተለያዩ ግዙፍ ግንባታዎችን በኢትዮጵያ በማከናወን በሁለቱ ሀገራት መካከል ጥብቅ መስተጋብር እንደፈጠረ ሲገለጽ ቆይቷል።
ከሰሞኑ የፈረንሳይ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደጣልያን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ”Webuild Group” ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር በሮም መወያየታቸውም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተዘገበ ገዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር በሮም ተገናኝተን እየተሳተፉባቸው ባሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ተወያይተናል ብለዋል።
አያይዘውም በጥቂት ወራት ውስጥ በሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት በሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ እንዲሁም በኮይሻ ግድብ ፈጣን አፈፃፀም እንደታየው ሀገራዊ ግቦቻችንን በማሳካት ረገድ ከኩባንያው ጋር ያለን ትብብር ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ውይይታቸው የረጅም ጊዜ ልማትን በመደገፍ ሀገር የሚያሻግሩ ፕሮጀክቶችን በመከወን ረገድ ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት ያንፀባረቀ እንደነበርም ተመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሮም ቆይታቸው ከመሰረተ ልማት ዕድገት ባለፈ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለመ ውይይትም ከሮማው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ አስራ አራተኛ በቫቲካን ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በማጠናከር ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒን ጋር በሮም ፓላዞ ቺጊ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ጣልያን መካከል የሁለትዮሽ ትስስሩን በማጠናከር ለአዲስ ኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ዕድሎችን በመፍጠር ላይ ያተኮረ ውይይት እንደነበርም ነው ያመላከቱት።
ውይይቱም በተለያዩ መስኮች እየተጠናከረ ለመጣው የኢትዮ-ጣልያን ግንኙነት መሰረት የሚጥል መሆኑንም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች መግለጻቸውን የጣልያን መገናኛ ብዙሃን ጭምር ዘግበውታል።
ለሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ሚና የሚያበረክተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአውሮፓ ጉዞም ፍሬያማ ውጤቶችን እያስገኘ ስለመሆኑም ከወደ ሮም የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በጌትነት ተስፋማርያም
#EBC #EBCdotstream #Ethio-Italian