ሕንድ እና ፓኪስታን ለድሮን ምርት ሚሊዮን ዶላሮችን መድበው ለውጊያ መጠቀም መጀመራቸው ተነግሯል።
ባለፈው ዓመት ለመከላከያቸው 96 ቢሊዮን ዶላር የመደቡት ሀገራቱ የድሮን ፉክክር ውስጥ ገብተዋል።
ለአስርት ዓመታት በጄቶችና ሚሳኤሎች ተኩስ ሲለዋወጡ የቆዩት የፓኪስታኗ ዋና ከተማ ኢስላማባድ እና የሕንድ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ በግንቦት ወር መግቢያ ለአራት ቀናት ባካሄዱት ውጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ድሮን ተጠቅመዋል።
ፓኪስታን ወደ ሕንዷ ጃሙ፤ ሕንድም ወደተለያዩ የፓኪስታን ወታደራዊ ይዞታዎች አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመላክ ጥቃት ማድረሳቸውን ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን የሁለቱን ሀገራት ባለስልጣናት ጠቅሶ አስነብቧል።
የአራት ቀናቱ ውጊያ በአሜሪካ ሸምጋይነት ቢበርድም ኒዩክሌር የታጠቁት ጎረቤቶች ወታደራዊ ዝግጁነታቸውን ለማሳደግ የመከላከያ በጀታቸውን አሳድገዋል።
ከዚህ በጀት ውስጥ የድሮን ግዢው ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ነው ዘገባው የጠቆመው።
ፓኪስታን ድሮኖችን ከቻይና እና ቱርክ ስታስገባ ሕንድ በራሷ አቅም ታመርታለች።
ኒው ደልሂ በቀጣይ አንድ ዓመት 470 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ዘመናዊ ድሮኖችን ለመታጠቅ አቅዳለች። ይህም ከቅርቡ ውጊያ በፊት የነበራትን የድሮን አቅም በሦስት እጥፍ ያሳድግላታል ተብሏል።
የኢስላማባድ የኤሮስፔስ ተቋምም ከቱርኩ ባይካር ጋር በመተባበር "ይሃ -III" የተሰኘ ድሮን በሀገር ውስጥ መገጣጠም ለመጀመር መቃረቧ ተነግሯል።
ሁለቱ ሀገራት ድሮኖችን ለውጊያ መጠቀም የጀመሩት "የለየለት ጦርነት እንዳይነሳ ወታደራዊ ጫናን ለመፍጠር በማሰብ ነው" ይላሉ በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዋልተር ላድዊግ።
ድሮኖች የተቀመጠላቸውን ዒላማ ነጥለው ከመምታትና የንፁሃን እና መሰረተ ልማቶችን ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ያላቸው ድርሻም ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው አንስተዋል።
የውድ አውሮፕላኖች እና አብራሪዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል ይልቅ በአነስተኛ ዋጋ የሚመረቱ ድሮኖችን መጠቀም ይሻላል ያሉት ሕንድ እና ፓኪስታን በቴክኖሎጂው ፍጥጫቸው እንዳያንር ተሰግቷል።
ከሕንድ ጋር 1 ሺህ 700 ኪሎሜትር የምትዋሰነው ፓኪስታን ከ36 በላይ የሚሆኑ የሕንድ የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶችን ለመምታት ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ድሮኖችን አሰማርታ ነበር።
ሕንድ አብዛኞቹን የፓኪስታን ድሮኖች መትታ መጣሏን ብትገልፅም፣ ቀላል የማይባል ጉዳት እንደደረሰባት ተገልጿል። ኒው ደልሂም በርካታ የእስራኤልን "ሀሮፕ"፣ የፖላንዱን "ዋርሜት" እና በራሷ ኩባንያ የሰራቻቸውን ድሮኖች ወደ ኢስላማባድ በመላክ ጥቃት ፈፅማለች።
ሁለቱም ሀገራት በድሮን ጥቃት ድል ቀንቶናል ሲሉ ተደምጠዋል። በርካታ ድሮኖችን ቢያጡም በፍጥነት በእጥፍ እየጨመሩ ለግጭት ዝግጁ ማድረግን መርጠዋል።