'አካማል' የእርቅ አደባባይ

1 Day Ago 152
'አካማል' የእርቅ አደባባይ
የባሕህል ሙዚየም በሆነችው ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት ቢጓዙ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የተለያዩ ባሕላዊ ክዋኔዎችን ያገኛሉ፡፡
 
ታዲያ በመኖር ሂደት ውስጥ በሰዎች መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ ማህበረሰቡ ግጭቶችን የሚፈታበት የየራሱ መንገድ አለው፡፡
 
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ የአሪ ዞን ነው፡፡ ዞኑ በግብርና ዘርፍ የሚተዳደር ሲሆን በዘርፉም ሰፊ አቅም ያለው አካባቢ ነው፡፡ በክልሉ ካሉ 32 ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የአሪ ብሔረሰብ አንዱ ነው፡፡
 
በአሪ ብሔረሰብ በርካታ ክዋኔዎች ይደረጋሉ፤ ከነዚህ መካከል ባሕላዊው የግጭት አፈታት ሥርዓታቸው አንዱ ነው፡፡
ይህ ክዋኔ የሚመራው ማህበረሰቡን በሚመሩ ባሕላዊ አባቶች ወይም ባላባቶች አማካኝነት ሲሆን የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓቱም 'ቄሽሚ' ይባላል፡፡
 
በደቡብ አሪ ወረዳ ኤይዳ ቀበሌ የሴኪ ባላባት ስፋራ ተገኝተናል፤ በዚህ ስፍራ የማህበረሰቡን ሰላማዊ ኑሮ የሚፈትኑ እና አብሮነት የሚያደፈርሱ ነገሮችን ሲፈጠሩ እንዴት ይፈታል? የሚለውን እንመለከታለን፡፡
 
በሁለት ግለሰቦች መሐል ከበድ ያለ ያለ ግጭት ተፈጥሯል፤ የአካባቢው ሰዎች ችግሩን ለመፍታት ቢሞክሩም ከችግሩ ክብደት በመነሳት በአንድ እና በሁለት ሰው ወይም በሰፈር ሽማግሌ በእርቅ የሚያልቅ ጉዳይ አለመሆኑን አዳምጠዋል፡፡
በመሆኑም ከፍ ወዳለ ደረጃ ወደ 'አካማል' ስፍራ ወደ አካባቢው ባለአባት የተጋጩትን ሰዎች ይዘዋቸው መጥተዋል፡፡ 'አካማል' የእርቅ አደባባይ እንደማለት ነው፡፡
 
በአሪ ብሔረብ የሽምግልና ደረጃዎች ቀለል ያሉ ጉዳዮች ሲገጥሙ እዛው በሰፈር እና በአካባቢው ሽማግሌዎች ይፈታሉ፡፡ 'ባቢ' ወይም የሰፈሩ ባላባት ግን የሁሉም የበላይ ነው፤ ስለሆነም እርሳቸው የሚወስኑት ውሳኔ በማንኛውም የማህበረሰቡ አባል ሊሻር አይችልም፡፡
 
በስፍራው ለመሸማገል የመጡ ሰዎች ስለተፈጠረው ጉዳይ በሚናገሩበት ወቅት መዋሸትም ሆነ ማታለል አይችሉም፤ የተጋጩትን ሰዎች ይዟቸው የመጣው ሽማግሌ ስለ ፀቡ መነሻ እና አጠቃላይ ሁኔታ ያስረዳል፡፡
 
በዳዮችም ሆኑ ተበዳዮች ለባላባቱ በአካባቢው ደንብ መሰረት ተንበርክከው እጆቻቸውን ደረታቸው ላይ በማድረግ ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡
 
ጉዳያቸውን ባላባቱ ካዳመጠ በኋላ በብሔረሰቡ ባሕል መሰረት እርቅ ይካሄዳል፡፡
 
እርቁ ከተካሔደ በኋላ በባሕሉ መሰረት የባላባቱ ባለቤት በማሕበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ኃይል እንዳላት የምትታመነውን 'ሳክታ' የምትባለውን ቅጠል በጎድጓዳ ዕቃ (ሾርቃ) ባለውኃ ውስጥ በመጨመር በአስፈጻሚው (ጎድሚው) ፊት ታስቀምጣለች፤ አስፈጻሚውም ከውኃው ይጎነጫል፡፡
 
ጎድሚው ቀምሶ ለባላባቱ ይሰጣል፤ ባለአባቱም ከቀመሰ በኋላ የጥፋቱ መሪ የሆነው ሰው እንዲጎነጭ ይሰጠዋል፤ ይህም ከልባቸው ይቅር መባባላቸውን የሚያረጋግጡት 'ሳክታ' የተነከረበትን የሾርቃ ውኃ በመቅመስ በመሆኑ ቀጥሎ እርቅ ላደረገው ሰው ይሰጠዋል፤ እርሱም በተመሳሳ ሁኔታ ከሾርቃው ውኃ ይጎነጫል፡፡
 
ግጭቱ በዚህ ምልኩ ከተፈታ በኋላ ቂም መያዝም ሆነ ዳግም ግጭት መፍጠር አይቻልም፡፡
 
እርቁ ሲጠናቀቅ የፀቡ መንስኤ ወይም ትልቅ ችግር ውስጥ ሊያስገባቸው የነበረው ጉዳይ ከዚህ በኋላ የጠብ መነሻ መሆን እንደማይገባው አባቶች ይናገራሉ፡፡
 
የተጣሉበት መሳሪያ አካፋም ሆነ ዶማ ለልማት እና ለመልካም ነገር ያገልግል ብለው አባቶች ይመርቃሉ፡፡
 
ትልቅ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ ግጭቶች በአሪ ብሔረሰብ ዘንድ በዚህ መልኩ ይፈታሉ፡፡
 
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
 

Feedback
Top