ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን መሰረት በማድረግ እያቀረበች ያለው የባሕር በር የማግኘት መብት ጥያቄ በሌሎች አጋር አካላት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ተናገሩ፡፡

በዓለም አቀፍ የንግድና አገልግሎት ግብይት ውስጥ ለመግባት የባሕር በር ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ምርቶችንና አገልግሎቶችን ወደ ውጭ ለመላክና ለማስገባት የባሕር በር የማግኘት መብት በዓለም አቀፍ ሕጉ በግልፅ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት ከ30 ዓመታት በላይ አይነኬ የነበረውን የባሕር በር መብት ጥያቄ አሁን በግልፅ አንስቷል፤ ህዝቡም በመሉ ልቡ የተቀበለውና የሚያምንበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ በባሕር ላይ የነበራትን ሚና ደግማ ለማሳካት ምንም የሚያስቀራት ነገር የለም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የባሕር በር ተጠቃሚ መሆናችን አይቀሬ ነው፤ ዓለም አቀፍ ሕጉም በአንቀፅ 60፣ 70፣ 124፣ 125 እና 127 ይደግፈናል ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው የቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ስብሰሰባ ላይም የባሕር በር ጥያቄው ጠላትም ወዳጅም እንዲያወቅ በግልፅ የማስረዳት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በ1982 ፀድቆ በ1994 ተግባራዊ እንዲሆን በተወሰነው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲሳካ በግልፅነት የቀረበ ፍትሃዊ ጥያቄ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ብሩክ፡፡
የባሕር በር አልባ የሆነችው ኡጋንዳ ከታንዛኒያ ጋር የጋራ ጥቅምን መሰረት በማድረግ ባደረገችው ስምምነት፣ የታንዛኒያን ወደብን ለማበልፅግ ተፈራርመው ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድና የባቡር ሃዲድ ግንባታ ለመጀመር ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብት በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ የሁሉንም ድጋፍ እንደምትፈልግ እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በላሉ ኢታላ