47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በወርሀ ጥር የተመረጡት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ ቃለ መሃላ በፈፀሙበት ዕለት ነበር አነጋጋሪ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የጀመሩት።
ወደ ሥልጣን በተመለሱበት በመጀመሪያው ቀን ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደ ኢሚግሬሽን፣ ንግድ፣ ኢነርጂ እና የፌዴራል የሰው ኃይል ፖሊሲዎች ያሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ትዕዛዞችን ማስተላለፋቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች ወደ መተግበር መግባታቸውን በርካቶች ታዝበዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አነጋጋሪ እርምጃዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የትኞቹ ናቸው?
ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የመውጣት እርምጃ
የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንድትወጣ የሚያስችል ትዕዛዝ እ.አ.አ. ጥር 20 ቀን 2025 መፈረሙን በርካቶች ኮንነውታል።
ይህም ለድርጅቱ ከፍተኛውን የገንዘብ መዋጮ የምታዋጣው አሜሪካን ወጪ ለመቆጠብ ታስቦ ትራምፕ ያደረጉት መሆኑ ሲነሳ ቆይቷል።
በዚህ ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማማተር የተለያዩ ሀገራትን በር እያንኳኳ መሆኑን አሳውቋል።
አሜሪካ ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት በድጋሚ መውጣቷ
የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት በድጋሚ እንድትወጣ የሚያስችል የአስፈጻሚ ትዕዛዝ መፈረሙ ይታወሳል።
ይህም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይጨነቁ መሪ በሚል በበርካቶች ዘንድ እንዲተቹ አድርጓቸዋል።
በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) ላይ የተጣለ ማዕቀብ
የትራምፕ አስተዳደር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) አባላት ላይ ፍርድ ቤቱ በሚያደርጋቸው ምርመራዎች ምክንያት ማዕቀብ መጣሉን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ይህም የአውሮፓውያን መጠቀሚያ ሆኗል በሚል ለሚተቸው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዱብዕዳ ያክል መሆኑን የዘርፉ ተንታኞች ገልፀዋል።
ከየመን ሁቲ አማፅያን ጋር የተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት
በኦማን አደራዳሪነት በአሜሪካ እና በየመን ሁቲ አማፅያን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት እ.አ.አ. ግንቦት 6 ቀን 2025 ሥራ ላይ መዋሉን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ይህም ያልተጠበቀ እንደነበር በርካቶች የተስማሙበት ጉዳይ ነው።
የውጭ ዕርዳታ ቅነሳ
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለተለያዩ ሀገራት የምታቀርበውን እርዳታ በመቀነስና በማቋረጥ ይታወቃሉ።
በተለይ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ)ን በጀት በማቋረጥ ሲሰራ በነበራቸው ሥራዎች ላይ ጥያቄዎችን ሲያነሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ዩኤስኤይድ ለተለያዩ ሀገራት የሚሰጠውን ዕርዳታ በመቀነሱ በርካታ ሰራተኞች ስራቸውን እያጡ ሲሆን፤ የዕርዳታ ተጠቃሚዎችም ችግር ላይ እየወደቁ መሆኑን የተባበሩተ መንግስታት ድርጅት ጭምር ሲገልፅ ቆይቷል።
ይህ ብቻም አይደለም የትራምፕ አስተዳደር ለሚሰነዘሩበት ወቀሳዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ ይመስል አሜሪካ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም እንደምትወጣ እየገለፀ ይገኛል።
በአውሮፓ ህብረት ምርቶች የታቀደው የ50 በመቶ ቀረጥ
የትራምፕ አስተዳደር በአውሮፓ ህብረት (EU) ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ ተጨማሪ የ50 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ዝተዋል። ይህም ከአውሮፓ ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚያላላ በመሆኑ በርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ሆኗል።
ከአሜሪካ ውጪ በሚመረቱ አይፎኖች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ መዛታቸው
የትራምፕ አስተዳደር አፕል ኩባንያ አይፎኖችን በአሜሪካ ውስጥ ካላመረተ በውጭ ሀገር በሚመረቱት ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥል አስጠንቅቋል።
ሃርቫርድ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል የተጣለበት እገዳ
የትራምፕ አስተዳደር ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይመዘግብ ለማገድ እርምጃ መውሰዱ ከሰሞኑ ወዝግብ ያስነሳ ጉዳይ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ጭምር አስታውቋል።
በምላሹ ዩኒቨርስቲው ነፃነቴን ተጋፍቷል በሚል የትራምፕ አስተዳደርን በመክሰስ ውሳኔውን ማሳገዱን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ይገኛል።
በመንግሥታዊ አስተዳደር ወጪ ቅነሳ ላይ ያተኮሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዚህም የባሱ ዉሳኔዎችን ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ሀገራት የየራሳቸውን ዝግጁነት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ በእንግሊዝ ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የደኅንነት ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ኤድ አርኖልድ ለቢቢሲ ሙያዊ ትንተናቸውን አቅርበዋል::
በጌትነት ተስፋማርያም
#Ebc #Ebcdotsream #USA #Trump #America