የአንጋፋው ዲፕሎማታችን ሰርጌይ ላቭሮቭ ዕውቀት እና ልምድ ሀገራችንን ክብር አጎናጽፏታል - ፕሬዚዳንት ፑቲን

4 Days Ago 211
የአንጋፋው ዲፕሎማታችን ሰርጌይ ላቭሮቭ ዕውቀት እና ልምድ ሀገራችንን ክብር አጎናጽፏታል - ፕሬዚዳንት ፑቲን
 
የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ተሰጥኦ፣ ዕውቀት፣ ልምድ እና የአዕምሮ ጥንካሬ ሩሲያንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሩሲያ ወዳጆችን የማይናወጥ አክብሮት ማጎናጸፉን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ይህን የተናገሩት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሩሲያውያን፤ የሩሲያ ፌደሬሽን መንግሥት ከፍተኛ የክብር ሽልማት ሥነ ሥርዓት በክሬምሊን ሴንት ካተሪን አዳራሽ በካሄዱበት ወቅት ነው።
የክብር ሜዳሊያው ከተበረከተላቸው መካከል በወታደራዊ አገልግሎት፣ በሕዝብ አገልግሎት፣ በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ፣ በከፍተኛ የመንግሥት አመራርነት፣ የኪነ-ጥበብ እና ባህል፣ በጤና ዘርፍ፣ በኢንዱስተሪ እና በሌሎች ዘርፎች ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዜጎች ይገኙበታል።
ዜጎችን የማክበር ልማድ ኪነ ጥበብን ጨምሮ በሁሉም ሙያዎች ውስጥ ያሉ ዜጎች ለሀገራቸው የሚችሉትን እንዲያበረክቱ የሚያነሳሳ መሆኑን ያወሱት ፑቲን፥ የዛሬው የክብር ሽልማትም ተሸላሚዎቹ በስኬታቸው በሕዝብ ፊት እውቅና ያላቸው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው ብለዋል።
"የክብር ሽልማቱ እናንተ ሩሲያ በነጻነት እና በክብር እንድትኖር፤ ለሀገራችን መጻኢ ብሩህ ተስፋን ለፈነጠቀው የጀግንነት ተግባራችሁ የኩራት እና የጥልቅ ምስጋና ዕውቅና ነው" ብለዋል።
የክብር ሽልማቱ ከተበረከተላቸው መካከል አንጋፋው የሩሲያ ዲፕሎማት ሰርጌይ ላቭሮቭ የሚገኙበት ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ያላቸውን አድናቆት በልዩ ሁኔታ ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድ ከእኚህ በሩሲያ ጥቅም ከማይደራደሩ ባለ ፅኑ አቋም ዲፕሎማት መማር እንዳለበት ጥሪ ያቀረቡት ፑቲን፥ ላቭሮቭ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሩሲያን ጥቅም ለማስከበር ባላቸው ቁርጠኝነት ደከመኝ ሳይሉ ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ውስብስብ በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ የሀገራቸውን ጥቅም ሲያስከብሩ መኖራቸውንም ፑቲን አስታውሰዋል።
ላቭሮቭ ለሀገራቸው ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦም ለክብራቸው የሚመጥነውን የሴንት አንድሪው አንደኛ ደረጃ ሽልማት ሊያገኙ መቻላቸውንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።
በለሚ ታደሰ
 

Feedback
Top