ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙት የፋይናንስ ምርመራ ውጤቶች

4 Days Ago 191
ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙት የፋይናንስ ምርመራ ውጤቶች
 
ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 780/2005ን ማውጣቷ ይታወሳል።
በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የፋይናንስ ደህንነት የማጣራት ስራዎች በርካታ ሃብት ከወንጀለኞች ማስመለስ እንደተቻለ ሲገለጽ ቆይቷል።
በሀገራችን በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና መሰል ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የተሰኘው ተቋም ነው።
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳለ አሰፋ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ከተቆጣጣሪና ከሕግ አስከባሪ ተቋማት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የፋይናንስ ወንጀሎችን በመከላከል ሥራ ጠንካራ ትብብር መስርቷል።
በተለይም የተለያዩ አጠራጣሪ የገንዘብ ዝውውርና ተያያዥ መረጃዎችን በተመለከተ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ ተቋማት ሪፖርቶችን ተቀብለን እናጣራለን ብለዋል።
አቶ እንዳለ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ከተለያዩ አካላት በተለያየ አግባብ የሚደርሱትንና ከልዩ ልዩ ምንጮች የሚያገኛቸውን መረጃዎች መነሻ በማድረግ በሁለት መልኩ የኢተለጀንስ ውጤት አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው ያስተላልፋል።
የመጀመሪያው አጠራጣሪ ግብይት መረጃዎችን መነሻ የሚያደርግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ የመረጃ ድጋፍ ጥያቄዎችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ነው የተነገሩት።
ጥቆማዎቹ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከንግድና የሙያ ማህበራት፣ ከግለሰቦችና ከተለያዩ ምንጮች የሚገኙ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት አገልግሎቱ 4 ሺህ 125 የአጠራጣሪ የግብይት መረጃዎችን መቀበሉን አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ ትንተና ያከናወነባቸውን 133 የፋይናንስ ምርመራ ውጤቶች በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለሚገኙ የሕግ አካላት ያስተላለፈ ሲሆን፤ የፋይናንስ ምርመራ ውጤቶቹ የ 567 ተጠርጣሪዎችን መረጃም ያካተቱ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙ የፋይናንስ ኢንተለጀንስ ምርመራ ውጤቶች ለሚመለከታቸው አካላት መተላለፋቸውን አስታውቀው፤ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ሰፊ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።
የታክስ ማጭበርበር፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገወጥ የገንዘብና የሰዎች ዝውውር፣ ሙስና፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት፣ ማጭበርበር እና ሌሎች ወንጀሎች ላይ ማጣራት መደረጉንም አስረድተዋል።
አቶ እንዳለ እንደተናገሩት፤ በተደረጉት የፋይናንስ ምርመራዎች የተለያዩ ክልሎች በታክስ ስወራ ምክንያት ሊያጡት የነበረን ከ990 ሚሊዮን በላይ ብር ማግኘት ችለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሂደት ላይ ያሉትን የፋይናንስ ምርመራዎች ሲጨምር ደግሞ መንግስት በታክስ ስወራና ማጭበርበር ሊያጣው የነበረ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ማዳን እንደሚቻል አመላክተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብ ወንጀል ጋር በተያያዘ በተደረገ ምርመራ ተመላሽ እንዲሆን የተደረገና ለማስመለስ በሂደት ላይ ያለ በጥቅሉ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መኖሩንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል አገልግሎቱ ለባለድርሻ ተቋማት የፋይናንስ መረጃ ድጋፍ መስጠቱን ጠቁመው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከሙስና፣ ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ 233 የመረጃ ድጋፍ ጥያቄዎች ቀርበው ድጋፍ ተሰጥቷል ብለዋል።
ምላሽ የተሰጠባቸው የፋይናንስ ኢንተለጀንስ የመረጃ ድጋፍ ጉዳዮች በውስጣቸው የ2ሽሲህ 216 ተጠርጣሪዎችን መረጃ የያዙ መሆናቸውንም አቶ እንዳለ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ የሕገወጥ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ከፀጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

Feedback
Top