ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

1 Day Ago 134
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር እና የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
 
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የጣልያን ከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ ፈርመውታል።
 
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በሁለቱ ሀገራት የተደረገው ስምምነት በትምህርቱ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።
 
በተለይም በትምህርት ዘርፉ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸው፤ የሚደረገው ድጋፍ ፍትሃዊና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
 
የትምህርት ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለውን ሥራ እና በትምህርቱ ዘርፍ ትብብር የሚሹ ጉዳዮችን ለሚኒስትሯ አብራርተውላቸዋል።
 
ሚኒስትር አና ማሪያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የጣሊያን አጋር መሆኗን አንስተው ሁለቱ ሀገራት በትምህርቱ ዘርፍ በላቀ ትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
 
የተፈረመው መግባቢያ ስምምነት በጣሊያን እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ቀጥተኛ ትብብር እንዲኖር የሚያበረታታ ነው ተብሏል።
 
ከዚህም በተጨማሪም በጣልያን መንግስት እና የአፍሪካ ቀንድ ባለብዙ ሃገራት (UNOPS) አጋርነት በኢትዮጵያ ለሚገነቡ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መግባቢያ ስምምነትም ሁለቱ ሚኒስትሮች በተገኙበት ተፈርሟል።
 
ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ኦግስቲኖ ፖሌሲ እና የአፍሪካ ቀንድ ባለብዙ ሃገራት ቢሮ ዳይሬክተርና የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን መፈረማቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

Feedback
Top