የክረምት ድባቴ ምንድነው?

1 Mon Ago 567
የክረምት ድባቴ ምንድነው?

የክረምት ወር ሲመጣ ብርድ እና ቅዝቃዜው እንደማይቀር ሁሉ ዝናቡ እና ጭቃው በተለይ ለከተሜው ምቾት የሚነሳ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህም ይመስላል ክረምት የድብርት ስሜት የሚበዛበት ነው የሚባለው፡፡

ይሄ ሃሳብ እውነት ነው ወይ በሚል ኢቢሲ ሳይበር ያናገራቸው የሥነ ልቦና ባለሞያ ሀናዲ የሱፍ እውነታውን አስምረው የክረምት ድባቴ የወቅታዊ ተጽዕኖ እክል “Seasonal Affective Disorder” የሚባለው እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም ጊዜያዊ የሆነ እና በሆነ ጊዜ አንዴ የሚመጣን የስሜት መዛባት የክረምት ድብርት እንለዋለን ብለዋል፡፡

ይህ የድብርት ስሜት በዓመት አንድ ጊዜ የሚከሰት ሲሆን ይህም ክረምት ላይ መሆኑን የሚጠቁሙት ባለሞያዋ፤ ለዚህ ድባቴ መነሻው “የፀሐይ ብርሃን በመቀነሱ ሰውነታችን ላይ የሚያመጣው ተጽንዖ” እንደሆነም ተናግረዋል።

ክረምት ሰውነታችን ጥሩ እንዲሰማው የሚያደርጉትን ስሜቶች እንዲጠፉ ያደርጋል የሚሉት ባለሞያዋ፤ ትንሽ ፀሐይ በወጣ ቁጥር የድባቴም መጠን እየቀነሰ ይሄዳል ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ ይህ ስሜት አይሎ በዚህ ስሜት ውስጥ የሆኑ ሰዎች ቀጣይነት ያለው መከፋት፣ በሚያስደስቱ ነገሮች  አለመደሰት፣ የምግብ ፍላጎት መጨመር ወይም መቀነስ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡

በድብርት ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች ታዲያ አስፈላጊ ሰው አይደለሁም ብሎ ማሰብ፣ የሰውነት መጨመር፣ ራስ ምታት፣ የወገብ እና የጨጓራ ህመምን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ እንደሚሆኑም ባለሞያዋ ተናግረዋል።

ከዚህ አልፎም ሞትን መመኘት የሚያስከትል ነው የሚሉት ባለሞያዋ፤ ድባቴ ትኩረት ካልተሰጠው ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያለው የስሜት ችግር ሲከስት “ላይት ቴራፒ” የተባለ ህክምና ስለመኖሩ የሚናገሩት ባለሞያዋ፤ በኢትዮጵያ ይህ አይነቱ ህክምና ያልተለመደ ቢሆንም ብርሃን ባሉባቸው ቦታዎች በመቀመጥ፣ ቴሌቪዥን ከፍቶ የፀሐይ ብርሃን ማየት እንደ “ቴራፒ” እንደሚያገለግል ገልጸዋል።

በክረምት ወቅትም መደበኛ የስፖርት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የእንቅልፍ ስርዓትን በማስተካከል እና ብዙ ጊዜ ውጪ በማሳለፍ ችግሩን መከላከል እንደሚቻል ባለሞያዋ ጠቁመዋል።

ከዚህ አልፎ ድብርቱ የተባባሰ ከሆነ ግን ወደ ህክምና ተቋም ሄዶ እገዛ ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ የሥነ ልቦና ባለሞያዋ ሀናዲ የሱፍ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በሜሮን ንብረት


Feedback
Top