ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

2 Mons Ago 800
ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ እና ቴዎድሮስ ንጉሴ ወልድሀዋሪያ በተባሉ ሀሰተኛ ስሞችን በመጠቀም ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው ሐሰተኛ ስሞቹን በመጠቀም ከሌሎች ግብረ-አባሮቹ ጋር በመሆን ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ በሚለው ስም ንግድ ፍቃድ በማውጣት፣ የወንጀል ድርጊቱ እንዳይደረስበት ለማድረግ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪው ከታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ክትትል ለመሰወር በቦሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመቀየር ህጋዊ በመምሰል የዕቃ እና አገልግሎት ግብይት ሳይኖር የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመለያ ቁጥር ርLB 0019300 ከሆነው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በ1 ሺህ 2 መቶ 70 ደረሰኞች አማካኝነት ምንም ሽያጭ ሳያካሄድ ደረሰኞችን ብቻ በመሸጥ መጠኑ 2,951,053,749.86 ብር የሚሆን ሽያጭ ማከናወኑም ተጠቁሟል፡፡

ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ባደረገው ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግዥ ፈጽመናል በማለት ሀሰተኛ ደረሰኞቹን ከተጠርጣሪው ላይ የገዙ ግብር ከፋዮች ደግሞ በሀሰተኛ ሰነዶች አማካኝነት ወጪያቸውን በማነር ለመንግሥት የሚከፈለውን ግብርና ታክስ እንዲቀንስና ያልተገባ ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ተመላሽ ከመንግሥት ካዝና አንዲወስዱ ማድረጉንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኢንተለጀንስ ሥራ ሂደት አስልቶ በላከው መሠረት ተጠርጣሪው ምንም ግብይትና አገልግሎት ሳይሰጥ ደረሰኞችን ብቻ በመሸጥ በመንግስት ላይ ያደረሰው ጉዳት መጠን፦

  1. የንግድ ትርፍ ግብር:- 769 ሚሊየን 890 ሺህ 1 መቶ ከ08 ሣንቲም፤
  2. የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) መጠን፦ 384 ሚሊየን 920 ሺህ 054 ብር ከ04 ሣንቲም ሲሆን፤

በአጠቃላይ በድምሩ 1 ቢሊዮን 154 ሚሊዮን 760 ሺህ 1 መቶ 62 ብር ከ12 ሣንቲም በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረሱም ተረጋግጧል።

ፖሊስ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈፍቃድ በማውጣት አያት ሆሴ ሪልስቴት በሚገኘው የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ፤ ስምንት ፍላሾችን፣ በተጠርጣሪው ሀሰተኛ ስሞችና በራሱ በተጠርጣሪው ትክከለኛ ፎቶግራፍ የወጡ እና የተዘጋጁ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችንም መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፤ ኅብረተሰቡም ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል ቀርቦ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።


Feedback
Top