በ1840ዎቹ እና 50ዎቹ በዓለም ላይ ፈተና ከደቀኑት በሽታዎች መካከል የእብድ ውሻ በሽታ አንዱ ነበር። በሽታው ገዳይ፣ የማይታከም እና ለመረዳት የሚቸግር መሆኑ ደግሞ ፈተናውን ውስብስብ አድርጎታል።
ሰዎችን ተስፋ አስቆርጦ የነበረው ይህ ስጋት እና ፈተና ግን በፈረንሳዊው የኬሚስትሪ እና ማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ ሉዊስ ፓስተር ሊለወጥ ችሏል።
ሉዊስ ፓስተር በ1878 በሕክምናው ዓለም ድንቅ የተባለለትን ክትባት በማግኘት በበሽታው በተጠቃ ውሻ የተነከሰ ጆሴፍ ሜይስተር በተባለ የ9 ዓመት ልጅ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞከሩት፡፡
ከ12 በላይ ንክሻዎች በሰውነቱ ላይ የነበሩበት ህጻኑ ሜይስተር ሕይወቱ ከባድ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረ ሲሆን፣ ሉዊስ ፓስተርም ሳያመነቱ ነው ጥናትና ምርምር ሲያደርጉበት የቆዩትን ክትባት ለልጁ የሰጡት፡፡
ለአስር ቀናት ተከታታይ 13 መርፌዎች በመስጠት ልጁን ማትረፍ የቻሉት ሉዊስ ፓስተር በዚህ ተአምር በተባለ ግኝታቸው ለሰው ልጆች እፎይታን ሊሰጡ ችለዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ክስተት የተፈፀመው ከ139 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 29 ቀን 1878 ዓ.ም የእብድ ውሻ በሽታ አስፈሪ የሞት ፍርድ በነበረበት ጊዜ ነው።
የፓስተር ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ግን ሕይወትን ማዳን ብቻ ሳይሆን የሕክምናውን ዘርፍ የለወጠ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡
የእብድ ውሻ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን፣ ቫይረሱ በበሽታው በተያዙ እንስሳት ምራቅ ውስጥ ይገኛል፡፡
እንደ ቀበሮ እና የሌሊት ወፍ ያሉ እንስሳት የቫይረሱ አስተላላፊ ሊሆኑ ቢችሉም በዓለም ዙሪያ በጣም የተለመደው የእብድ ውሻ በሽታ ተሸካሚ የሰው የቅርብ ጓደኛ የሆነዉ ውሻ ነው፡፡
አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ በኋላ ምልክቶቹ ወዲያውኑ የማይታዩበት ሲሆን፣ ቫይረሱ ወደ ማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት እና አንጎል እስኪደርስ ድረስ ከአንድ እስከ ሶስት ወራት በፀጥታ በሰውነት ውስጥ ሊቆይ ይችላል፡፡
ምስጋና ለሉዊስ ፓስተር ግኝት እንጂ በአሁኑ ወቅት በእብድ ውሻ በሽታ በተጠረጠረ እንስሳት የተነከሰ ወይም የተቧጨረ ሰው ክትባቱን ከወሰደ መቶ በመቶ ከበሽታው መዳን ይችላል፡፡
በበሽታ አምጪ ጀርሞች እና በምግብ መበላሸት ዙሪያ ባደረጉት ምርምር የሚታወቁት ሉዊስ ፓስተር ወተትን ደህንነቱ የተጠበቀ እና ትኩስነቱን ጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርገውን "ፓስቲዩራይዜሽን" የተባለዉን ዘዴም ፈልስፈዋል፡፡
የቢራ እና የወይን መበላሸትን በመከላከል ረገድም አበርክቷቸው የጎላ ነው፡፡
ከሉዊስ ፓስተር ግኝት በፊት ሐኪሞች እና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በዓይን ስለማይታዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡
ሆስፒታሎች ብዙ ጊዜ በቆሻሻዎች የተሞሉ እንደነበሩ፣ የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች ያለ ተገቢ ጽዳት እንደገና ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር እና ታካሚዎችም ለኢንፌክሽን ከማጋለጥ እስከሞት ይደርሱ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
ሉዊስ ፓስተር ማፍላት፣ ማሞቅ ወይም ኬሚካሎችን መጠቀም ጎጂ የሆኑ ረቂቅ ተህዋሲያንን ሊገድል እንደሚችል ለሕክምናዉ ዓለም አሳይተዋል፡፡
በዶሮ ኮሌራ በሽታ ባደረጉት ግኝትም የሚታወቁ ቢሆንም ፓስተር በሰው ጤና ላይ ትልቁን ተፅዕኖ ባሳደረው በእብድ ውሻ በሽታ ቫይረስ ላይ የሠሩት ሥራ የበለጠ ሲወደሱ ይኖራሉ፡፡
የሉዊስ ፓስተር ምርምሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በማዳን ለዘመናዊ ሕክምና መሠረት ጥለዋል ይላሉ አሜሪካዊቷ የአስትሮ ፊዚክስ ባለሙያ ኤሚ ሜንዘር፡፡
የሉዊስ ፓስተር ውርስ በዘመናዊው የሕክምና ዓለም ውስጥ በየቀኑ ይታያል፤ ሁላችንም አውቀንም ሆነ ሳናውቀው የእርሳቸዉ የሥራ ውጤት ተጋሪዎች ነን፡፡
የፓስቸራይዜሽን፣ የተዋህሲያን ፅንሰ-ሀሳብ፣ ዘመናዊ ክትባቶች እና የሆስፒታል ንፅህና ሁሉም ወደ ሉዊስ ፓስተር ይመሩናል፤ ምናልባትም ያለ ፓስተር ግኝቶች ብዙዎቻችን ዛሬ በሕይወት ላንኖር ሁሉ እንችል ነበር።
በ1878 ዓ.ም የመጀመሪያውን የተሳካ የእብድ ውሻ በሽታ ክትባት ከተሰጠ ከሁለት ዓመታት በኋላ የፓስተር ኢንስቲትዩት በፈረንሳይ ፓሪስ ተቋቋመ፡፡
ተቋሙም በኅብረተሰብ የጤና ችግሮች ላይ ሲሠራ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፤ የፖሊዮ፣ ሳንባ ነቀርሳ እና ኢንፍሉዌንዛ ላየ ትልልቅ ግኝቶችን አበርክቷል።
የፓስተር ኢንስቲትዩት ታሪክ በፈረንሳይ ብቻ አያቆምም፤ ባሕር ተሻግሮ በኢትዮጵያም የሉዊስ ፓስተር አሻራ ይታያል፡፡
የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከፈረንሳይ የፓስተር ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት በማድረግ "ኢንስቲትዩት ፓስተር ዲ ኢትዮፒ" ወይም "የፓስተር ኢንስትትዩት" በሚል የማይክሮ ባዮሎጂ ተቋም ተመሰረተ፡፡
የአሁኑ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የያኔው ፓስተር ኢኒስትትዩት በ1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተቋቁሞ የእብድ ውሻ በሽታን ጨምሮ በርካታ የኅብረተሰብ ጤና መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በሕክምናዉ ዘርፍ አሻራቸው ጎልቶ ከሚታዩት መካከል አንዱ የሆኑት ሳይንቲስት ሉዊስ ፓስተር ታኅሣሥ 18 ቀን 1815 ዓ.ም በፈረንሳይ ዶል ከተማ ነበር የተወለዱት፡፡
የሥራቸው መጀመሪያ የኬሚስትሪ ባለሙያነት ቢሆንም ወደ ማይክሮባዮሎጂዉ ዓለም ፊታቸውን አዙረው ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ለመሆን በቅተዋል፡፡
መስከረም 18 ቀን 1888 ዓ.ም በሞት የተለዩት ሉዊስ ፓስተር ስማቸው እና ሥራቸዉ ሲዘከር ይኖራል፡፡