ሸዋረገድ ገድሌ - የሀገር ጋሻ

11 Hrs Ago 84
ሸዋረገድ ገድሌ - የሀገር ጋሻ

ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶች ከፖለቲካው ቢገለሉም አጥሩን ጥሰው ‘የጦር ግንባር’ ውስጥ እስከመሳተፍ ደርሰው ለሀገራቸው ሲሉ በጀግንነት ታግለዋል፣ ታስረዋል፣  ሞተዋል።

ከነዚህ ጀግኖች ሴቶች መካከል ታዲያ በተለይ በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ጀብዱ የፈፀሙት ሸዋረጋድ ገድሌ አንዷ ናቸው።

ሸዋረጋድ ገድሌ በ1878 ዓ.ም በደብረ ብርሃን አከባቢ እንደ ተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የፋሺስት ጣሊያንን ጦር ለመዋጋት በአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር ሲከናወን የነበረውን የአገልግሎት ምዝገባ ፈፅመው የአርበኝነት ሕይወታቸውን ጀመሩ።

በወቅቱ ለሠሩት የጀግንነት ሥራም፦

የምታስፎግር ሰንጋ ገለሌ

በጦር መካከል ሳይሆኑ አያሌ

በጥይት ገዳይ ነጭ ብርገሌ

የሴት ወንድ ናት ሸዋረገድ ገድሌ… ተብሎ ተገጥሞላቸዋል።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ለ5 ዓመታት በወረረበት ወቅት ሸዋረገድ ከአባታቸው ፊታውራሪ ገድሌ የወረሱትን መሬት በመሸጥ ገንዘቡን ለወታደሮች እና ለአርበኞች ልብስ፣ መድኃኒት፣ ጥይት እና ሽጉጥ እንደገዙ ይነገራል።

በተጨማሪም ለቀይ መስቀል የገንዘብ ድጋፍም ይሰጡ የነበረ ሲሆን ይህ ተግባራቸውም በጣሊያኖች እንዲከሰሱ አንዱ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ለሀገራቸው ነፃነት ለመሞት ቆራጥ የነበሩት ሸዋረገድ፣ ከእርዳታ ባሻገር  የአርበኞች የመረጃ ምንጭም ነበሩ። በከተማዋ የሚሰሙ መረጃዎችን ለአርበኞች በመላክ እጅጉን ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ በብዛት ተጽፏል።

ሸዋረገድ በጀግንነት በተዋጉበት ጊዜያት ተይዘው ዛፍ ላይ ታስረዋል፤ ክፉኛ ተደብድበው ወደ እስር ቤት ወርደዋል፤ የማደጎ ልጃቸው ዐይናቸው ፊት ሲገደል አይተዋል፤ የሞት ፍርድም ተፈርዶባቸው በሰዎች ልመና እና ተማፅኖ ወደ እስር ተቀይሮላቸዋል።

ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አገግመው በማምለጥ የጣሊያንን ወረራ እስከ መጨረሻው ተዋግተዋል። ሸዋረገድ ከዚህም ያለፈ ተነግሮ የማያልቅ ጀብድ ሠርተዋል።

በመጨረሻም በ1933 ከአምስት ዓመት በኋላ የጣሊያን ወራሪ ኃይል በጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ተሸንፎ ከሀገር ተባረረ።

የፋሺስት ጣሊያን ራስ ምታት ሆነው ስማቸውን በጀግንነት መዝገብ በደማቅ  የጻፉት ሸዋረገድም ሙሉ በሙሉ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሰማሩ።

ከዓመታት በኋላም በጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የመሞታቸውን ዜና የሰሙም፦

እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ

እናንት ሥጋ ቤቶች ሥጋውን ምረጡ

ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ

ቤተሰቧ ሰፊ ገና እና ጥቅምት

ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት? … ሲሉ በግጥም አልቅሰውላቸዋል።

ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት በዘመናቸው የሚጠበቅባቸውን የአርበኝነት ሚና በመወጣት ታላቋን ኢትዮጵያ ከትውልድ ትውልድ አሸጋግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም ጊዜው የሚጠይቀውን አርበኝነት የሚፈፅሙ ሸዋረገዶችን የማፍራት ኃላፊነት አለበት።

በሴራን ታደሰ


Feedback
Top