የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ ሐውልት

13 Hrs Ago 206
የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ ሐውልት

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጅምሮ ሀገራቸውን ሊወርር የመጣውን ጠላት በአንድነት እና በጀግንነት ቆመው መክተው ነፃነታቸውን እንደጠበቁ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

በዚህ የጀግንነት ተጋድሎ ውስጥ ታዲያ በርካታ ጅግኖችም ተሠውተዋል።

የጣሊያን ጦር በዓድዋ ድል ለደረሰበት ሽንፈት የበቀል ጦሩን ስሎ ከ4 አስርት ዓመታት በኋላ በተደራጀ የጦር መሣሪያ ታግዞ እና አቅሙን አጠናክሮ ተመልሶ መጣ።

በዚህም ወቅታዊ የበላይነት ይዞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ከተሰቀለበት አወረደ።

የኢትዮጵያ አርበኞችም ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ ወራሪውን ኃይል አሸንፈው ልክ በ5 ዓመቱ በተመሳሳይ ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ዳግም የሀገራቸውን ዳር ድንበር አስከብረው ለነፃነታቸው የተዋደቁለትን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ አድርገው ሰቀሉ።

የአባት አርበኞች ደማቅ አሻራ ያረፈበት በ4 ኪሎ አደባባይ የሚገኘው የድል ሐውልትም ለዚህ ደማቅ የድል ታሪክ መታሰቢያ ተደርጎ ቆመ።

ይህ የአርበኞች ድል ሐውልት የተቀረጸበትን መንግድ፣ በውስጡ የያዛቸውን ነገሮች እና ትርጉማቸውን እንመልከት።

ሐውልቱ ጥቅምት 23 ቀን 1936 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን መታሰቢያነቱም ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ሕይወታቸውን ለሠዉ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሆነው ለነፃነታቸው ሳይታክቱ እና ተስፋ ሳይቆርጡ ለታገሉ አርበኞች ነው።

ከበሀ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተቀረፀው ሐውልቱ ከሥር 6 በሮች ያለው ክብ ቅርጽ ሲሆን መሐል ላይ ደግሞ የአክሱም ሐውልትን ከክቡ ውስጥ እናያለን።

በስድስቱም በር በተለያየ ሁኔታ እና መልክ ለሀገራቸው ዋጋ በከፈሉ አርበኞች ምሳሌነት የተቀረፁ ምሥሎች እንዲሁም መልዕክት እና ምልክቶች ሰፍረውበት ይገኛሉ።

መልዕክቱ ኢትዮጵያውያን በ5ቱ ዓመታት የጣሊያን ወረራ ጊዜ በተለያየ ስፍራ ሆነው ለነፃነት የከፈሉትን ዋጋ ማሳያ ነው።

ከእነዚህ መካከል በጠላት መሐል ተቀምጠው በራሳቸው ላይ የሞት ጥላ እያንዣበበ ጠላትን ይሰልሉ የነበሩ እንዲሁም ጥይት፣ ስንቅ እና መድኃኒት ሲያቀብሉ የነበሩ፣ ሀገራቸውን በስውር ላገለገሉ መታሰቢያ ተቀርፆላቸዋል።

አምስት አምታቱን በስደት በሰው ሀገር ያሳለፉ፤ ያለ ሀገር በክብር እና በነፃነት አለመኖሩን ተረድተው ለኢትዮጵያ ሲከራከሩ እና ሲታገሉ ለነበሩትም እንዲሁ መታሰቢያ ተደርጎላቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በስደት በነበረበት ጊዜ ለመንግሥታቱ ድርጅት (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የጣሊያንን ወረራ እንዲያወግ እና እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀው ነበረ። ሆኖም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

በሌላኛው በር ሐውልቱ ላይ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእጃቸው ባንዲራ ይዘው፣ የይሑዳ አንበሳ ደግሞ ከእግራቸው ሥር ተቀምጦ ይታያል። ይህ የተቀረፀው ንጉሠ ነገሥቱ ላደረጉት ተጋድሎ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የእሾህ አክሊል የያዘች ሴት ምሥል የተቀረፀላቸው፣ ለሀገራቸው ነፃነት አምስት ዓመታት በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱ እና ዋጋ ለከፈሉ በሙሉ ያሳለፉትን መከራ ለማሰብ የቆመ መታሰቢያ ነው።

ክቡ እላዩ ላይ ሙሉ ጽሑፍ የሰፈረበት ደግሞ ከእምነበረድ የተቀረፀ ሆኖ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከአምስት ዓመት የስደት ሕይወት በኋላ በ1933 ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መንበረ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ሚያዝያ 29 ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉት ንግግር ሰፍሮበት ይገኛል።

በክቡ መሐል ላይ የቆመው የአክሱም ሐውልትን ቀና ብለን ስንመለከት መጨረሻ ላይ የሥርወ መንግሥቱ ምልክት የነበረው የይሑዳ አንበሳ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ይታያል።

ከአንበሳው ወረድ ብሎ የሚታየው ሰዓት ሲሆን 7 ሰዓት ላይ መሆኑ የሚያሳየው አርበኞች አዲስ አበባን የተቆጣጠሩት ከቀኑ 7:00 ላይ መሆኑን ለማመልከት ነው።

ሐውልቶች ዘመንን እና ታሪክን ከመግልጽ ባሻገር በወቅቱ የነበረውን ክፉ እና ደግ እንድናውቅ ይረዱናል። እኛም ክፉውን ላለመድገም፣ ደግ ነገሩን ደግሞ አልቀን ለመተግበር የመትጋት ኃላፊነት አለብን።

ሐውልቶች ያለፉ ታሪኮቻችን ማሳያ ከመሆናቸው ባሻገር ጀግኖቻችን የሚዘከሩባቸውም ጭምር ናቸው።

እንኳን ለ84ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ


Feedback
Top