የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ84ኛው የዐርበኞች ቀን መልዕክት

1 Day Ago 166
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ84ኛው የዐርበኞች ቀን መልዕክት
 
እንኳን ለ84ኛው የዐርበኞች (የድል) በዓል አደረሳችሁ።
 
ቀደምት እናትና አባቶቻችን ነጻነትን በደም አስከብረው ሀገር አውርሰውናል። በዚህም እንኮራለን። እነዚህ ቀደምት ዐርበኞች በከፈሉት ዋጋ ዛሬ ቀና ብለን በነጻነት ዐደባባይ እንድንራመድ አድርገውናል። በድህነታችንና በኋላ ቀርነታችን ምክንያት ግን ነጻነታችን ሙሉ ሊሆን አልቻለም።
 
ነጻነታችን የተሟላ እንዲሆን ዛሬ ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዘመን ዐርበኞች ትፈልጋለች።
 
የሁለተኛው ዘመን ዐርበኞች ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና በማድረስ ነጻነቷን ሙሉ የሚያደርጉ ናቸው። በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በሚኖረው ሰላማዊ ጦርነት፣ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ታግለው የሚያሸንፉ ዐርበኞች ናቸው።
 
የዚህ ዘመን ዐርበኝነት ትጥቁ ዕውቀት፣ ክህሎት እና ዲሲፕሊን ነው። ወኔው የሀገር ፍቅር፣ ቆራጥነት እና ንጽሕና ነው። ግቡ የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው።
 
ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ሁለቱም ዓይነት ዐርበኞች ያስፈልጋሉ። ይህ ዘመን ደግሞ ይበልጥ ሁለተኛውን አርበኝነት ይሻል። ይሄ ቀን የመጀመሪያውን ዐርበኝነት መዘከሪያ፤ ለሁለተኛው ዐርበኝነት ደግሞ መሰረት ማፅኛ እንደሚሆን ተስፋዬ የላቀ ነው።
 
መልካም በዓል ይሁን!
 
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Feedback
Top