የኦንላይን ሥራዎች ወይም ‘ሪሞት ጆብስ’ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሥራን በቀላል እና በተቀላጠፈ መንገድ ለመሥራት የሚያስችል ነው።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኦፕሬሽን ማናጀር ህሊና በላቸው፣ በኦንላይን የሚሠሩ ሥራዎች አማካኝነት 90 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የዜጎች ክህሎት ከማሳደግ አንፃር ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ማናጀሯ ለ"ኢቢሲ የሀገር ጉዳይ" ገልጸዋል።
በ'ኦንላይን' የሚሠሩ ሥራዎች ዜጎች እራሳቸውን አብቅተው የሚሠሩበት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ገፅታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው፤ ትላልቅ ዳታ ሴንተሮች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህም የሥራ ዕድልን ለማስፋት እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የ"ጤና ፈርስት" መሥራች እና ባለቤት አቶ አብረሃም አሰፋ፤ የ"ጤና ፈርስት" መተግበሪያ ከ2 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ መተግበሪያው አሁን ላይ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።
በመተግበሪያው አማካኝነት አንድ ሰው ቤቱ ሆኖ የሚፈልገውን የሕክምና ተቋም ወይም የሕክምና ባለሙያ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ይገልፃሉ።
"ጤና ፈርስት" መተግበሪያ 24 ሰዓት በከተማም ሆነ በገጠር ላሉ ታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚናገሩት አቶ አብረሃም፤ መተግበሪያው የሕከምና ምክር ብቻ ሳይሆን የላብራቶሪ ውጤት እንዲሁም የመድሃኒት ማዘዣን ከሕክምና ባለሙያ ማግኘት እንደሚያስችል ይናገራሉ።
የሶፍትዌር ኢንጂነሮቹ ወጣት ማለዳ ሞቱማ እና ወጣት አብዱላሀፊዝ መሐመድ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ላሉ ተቋማት የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
በዚህ የ‘ሪሞት ጆብስ’ ዘርፍ ተጠቃሚ የሆኑት ወጣቶቹ በኢኮኖሚ ትልቅ ለውጥ እንዳመጡም ተናግረዋል።
የዲጂታል ኮንስትራት ድርጅት መሥራች እና ባለቤት እዩኤል አብረሃም በበኩላቸው፤ ወጣቶች ሥራ የለም የሚለውን አመለካከት ወደ ጎን ትተው የሥራ ዕድልን ለራሳቸው ማመቻቸት እንዳለባቸው ይገልፃሉ።
ወጣቶች የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን አዳብረው ከራሳቸው አልፈው ለሀገር መጥቀም እንደሚችሉም ይናገራሉ።
አክለውም የ‘ሪሞት ጆብስ' ዜጎች እራሳቸውን አብቅተው በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራቸውን ገፅታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠቅሳሉ።
በሔለን ተስፋዬ