የሠራተኛው ትግል ከኢንዱስትሪ አብዮት እስከ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስጋት

16 Days Ago
የሠራተኛው ትግል ከኢንዱስትሪ አብዮት እስከ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስጋት

ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ የነበረበት 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሠራተኛው በርካታ የመብት ጥያቄዎችን ያነሳ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች መካከልም የተመጣጣኝ ከፍያ፣ የሥራ ሰዓት፣ የመደራጀት እና ሌሎች ይገኛሉ፡፡

በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ሕይወትን ማጣት፣ አካል መጉደል፣ ለዘላቂ የጤና ችግር መዳረግ እና ሌሎች ለሰው ልጆች ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ጥያቄው መሰረታዊ እንዲሆን ማድረጋቸውን የሠራተኛውን ትግል የሚያወሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  

ሠራተኞች ትግላቸውን ቀጥለው ምቹ ባልሆነ የሥራ አካባቢ ከ10 እስከ 16 ሰዓታት የነበረው የሥራ ሰዓት 8 ሰዓት ብቻ ሆኖ የሙሉ ቀን ደመወዝ እንዲከፈላቸው መጠየቅ ቢጀምሩም፣ የዘመኑ አሠሪዎቻቸው ግን ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አልፈለጉም ነበር፡፡

ይህ የከበርቴዎች ለሠራተኛው ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ግን ሠራተኞች የበለጠ ተደራጅተው ጥያቄያቸውን እንዲገፉበት አደረጋቸው:: ነገር ግን ቀጣሪዎቹ በማይመች አካባቢ እና የአየር ሁኔታ ውስጥ በቀን ለረዥም ሰዓታት በማሠራት ከፍተኛ ትርፍ ማጋበስ የለመዱ በመሆናቸው በቀላሉ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ 

በሠራተኛው እንቅስቃሴ የተበሳጩት እና መጪው ሁኔታ ያሳሰባቸው አሠሪዎች “አድማ ቀስቅሳችኋል፤ ምርታማ መሆን አልቻላችሁም፤ እኛ በምንፈልጋችሁ ሁኔታ እየሠራችሁ ስላልሆነ አንፈልጋችሁም” በማለት በርካታ ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበት ጀመሩ::

ይህ የአሠሪዎች ውሳኔ ብዙ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ሠራተኞችን መስዋዕትነትን ቢያስከፍልም የሠራተኛውን የተደራጀ ትግል ግን አላቆመውም፤ ሠራተኛው በተለያየ ጊዜ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጠው ሲቀር ፋብሪካዎችን እያቃጠለ፣ እርሻዎችን እያወደመ ንዴቱን ሲወጣ አሠሪዎቹም ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጠሉ፡፡

ሠራተኛው ጥያቄውን ከጀመረ ከ20 ዓመታት በኋላ የሶሻሊዝም ንቅናቄ ሲጀመር የሠራተኛው ትግል የተስፋ ጭላንጭል መመልከት ጀመረ::

“ሠራተኞች የምርቱ ተቆጣጣሪ፣ አከፋፋይ እና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው” የሚለው ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በሁሉም የዓለም ክፍል ያሉ ሠራተኞችን ማነቃቃት ጀመረ፡፡ በሚሊዮኖች ላብ ጥቂቶቹ የሚከብሩበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እየሞቱ እና እየቆሰሉ ጥቂቶች ትርፍ የሚያጋብሱበት ሥርዓት መለወጥ አለበት የሚሉት የሠራተኛው መደብ አባላት የሶሻሊዝምን ንቅናቄ እንደ አዲስ አማራጭ ማየት ጀመሩ፡፡

ይሁን እንጂ ከበርቴዎቹ የሠራተኛውን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ማፈን በመጀመራቸው በሥራ አካባቢ ያለው ሥርዓት አልበኝነት እየተባባሰ መጣ፡፡ ሥርዓት አልበኝነቱ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን በኃይል አስወግዶ ኢንዱስትሪውን እስከ መቆጣጠር እና መንግሥታት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ወደሚችል እንቅስቃሴ አደገ፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ዓላማን ይዘው የተነሱት የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች የሠራተኛውን መደብ ተጠግተው ነገሮችን በማቀጣጠል የሠራተኛው መደብ ጥያቄ ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዲይዝ አደረጉት፡፡

እ.ኤ.አ.ግንቦት 1 ቀን 1878 በመላው የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች በ13 ሺህ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ከ300 ሺህ በላይ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ:: በችካጎ ብቻ 40ሺህ ያህል ሠራተኞች ከፖሊስ ጋር ተፋጠጡ፡፡

አልበርት ፓርሰንስ፣ ጆን ሞስት፣ ኦገስት ስፒስ እና ሉዌስ ሊንግ የተባሉ የሠራተኛ መብት አቀንቃኞች ስማቸው ይነሳና ይወደስ ጀመር:: በችካጎ እና በመላው የአሜሪካ ግዛቶች ሰልፎች የሥራ ማቆም አድማዎች ተቀጣጠሉ:: ጥያቄው እየገፋ ሲመጣ ባለሥልጣናት እና ከበርቴዎች የሠራተኛውን መደብ ጥንካሬ እና የነውጠኞችን ከሠራተኛው መደብ ጋር መሰለፍ ተረዱት::

እ.ኤ.አ.ግንቦት 3 ቀን 1878 በሰልፈኞች እና አመጸኞች መካል ግጭት በመፈጠሩ ፖሊስ ሠራተኞችን እያፈነ በመውሰድ ማሰቃየት እና ማሰር ጀመረ:: አብዛኞቹ እስረኞች የብረታ ብረት ሠራተኞች ማኅበር አባላት ነበሩ:: ይህ አካሄድ ግን አመጹን ከመግታት ይልቅ አባብሶት የብረታ ብረት ሠራተኞች በታሠሩበት አካባቢ በተደረገው አመጽ ወደ 200 መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች በአንድ ጊዜ ከፖሊስ ጋር ገጥመው ሁለት ሠራተኞች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ:: ፖሊሶችም የአመጹን መሪዎች እና የሠራተኛው መብት ተሟጋቾችን ሰብስበው አሰሯቸው፡፡

መስከረም 12 ቀን 1880 ከእስረኞቹ መካከል ፓርሰን፣ ስፒስ፣ ኢንግል እና ፊሸር የተባሉት የሠራተኛው መደብ አቀንቃኞች በስቅላት ተቀጡ:: ሊዊስ ሊንግ የተባለው ተሟጋች ደግሞ እንደሚገደል ሲያውቅ ራሱን አጠፋ:: ፊልደን ኒቤ እና ሽዋብ የተባሉ የሠራተኛው መብት ተሟጋቾች ደግሞ ከስድስት ዓመታት እሥር በኋላ ተፈቱ::

በዚህ መልኩ በአሜሪካ የተቀጣጠለው የሠራተኛው የመብት ትግል እ.ኤ.አ. ግንቦት 1 ቀን 1989 (ሚያዝያ 23 ቀን 1880 ዓ.ም) የመጨረሻ ምዕራፍ አገኘ::

ሠራተኛው በቀን ለስምንት ሰዓታት ብቻ መሥራት እንዳለበት በመንግሥት እና በአሠሪዎች ታምኖ ጥያቄው ተቀባይነት አገኘ፡፡ እሁድ ብቻ የነበረው የሳምንቱ የዕረፍት ቀን ቅዳሜንም ጨመረ፡፡ በዚህ የተነሳ ሚያዝያ 23 ቀን የዓለም የሠራተኞች ቀን እየተባለ ለሠራተኞች መብት ሕይወት የከፈሉ ሰዎች የሚታሰቡበት ሆነ::

ኢትዮጵያን ጨምሮ 162 ሀገራት ዕለቱን ብሔራዊ በዓል አድርገው ያከብሩታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተለያየ መልኩ አስበውት ይውላሉ:: ከፍተኛ የሠራተኞች ተጋድሎ ተካሄዶባት ዕለቱ የተጀመረባት አሜሪካ ቀኑ ከታሪክ እንዲፋቅ ብዙ ጥረት አድርጋ የነበረ ቢሆንም ስላልቻለች ቀኑን ብሔራዊ በዓል ሳታደርግ እንዲሁ አስባ ትውላለች፡፡

በዓሉ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ135ኛ ጊዜ ሲከበር፣ በኢትዮጵያም ለ49ኛ ጊዜ ተከብሮ ይውላል። 

በስታታ መረጃ መሰረተ እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም ዙሪያ ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ተቀጣሪ ሠራተኞች በዓለማችን ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል 2.1 ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ፣ 1.4 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው። ይህም በ1991 ከነበረው 2.23 ቢሊዮን የሰራተኞች መጠን የአንድ ቢሊዮን ጭማሪ አለው። 

የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም እንደሚለው በቀጣዮቹ ዓመታት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ምክንያት 85 ሚሊዮን ሥራዎች ይቀነሳሉ። በሂደትም 300 ሚሊዮን የሚያህሉ የሙሉ ጊዜ ሥራዎች በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ እንደሚያዙ ተተንብዮአል። ሌሎች ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ይህ አኃዝ እስከ 800 ሚሊዮን አለፍ ሲለም እስከ 1 ቢሊዮን ሊደርስ ይችላል።

እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) መረጃ ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በበለጸጉ ሀገራት 60 በመቶ፣ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት 40 በመቶ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት 26 በመቶ ሥራዎችን ይተካል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top