ክልሉ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ በመስራት ላይ ይገኛል - አቶ ጥላሁን ከበደ

16 ቀን በፊት
ክልሉ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ በመስራት ላይ ይገኛል - አቶ ጥላሁን ከበደ

በኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የገቢ ምርትን 85 በመቶ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቀል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥትም በክልሉ ፈጣን ዕድገት በማስመዘገብ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ከሰጣቸው የልማት ዘርፎች አንዱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ ያለውን የመልማት ፀጋ በመለየትና አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ክልሉ ያለውን አቅም በመጠቀም እና የግል ዘርፉን በስፋት በማሳተፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን ለማሳደግ እና ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የኢንዱስትሪ ተቋማትን በክላስተር በማቋቋም ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከርና ማስፋፋት የክልሉ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሀብት ያፈሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን በኢንዱስትሪው ዘርፍ በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው ባለሀብቶች በክልሉ ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top