ሀሺሽ በማካሮኒ ውስጥ ደብቆ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞ ለመግባት የሞከረው ግለሰብ

3 ወር በፊት
ሀሺሽ በማካሮኒ ውስጥ ደብቆ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞ ለመግባት የሞከረው ግለሰብ
በምግብ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ደብቆ ተጠርጣሪ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
 
ግለሰቡ ከናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዞ፤ በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መሄዱ ተነግሯል።
 
በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ምግብ ይዞለት የሄደው ይኸው ተጠርጣሪ፤ ከድፍረትም ድፍረት የሚያሰኝ ተግባር መፈጸሙን ነው ፖሊስ የገለጸው።
 
እንደ ፖሊስ ገለጻ፥ በወቅቱ በሳህን የተቋጠረው ምግብ እንጀራ ፍርፍር በማካሮኒ ነበር፤ ምግቡን ፈትሸው የሚያስገቡት የፖሊስ አባላት በማካሮኒ ቀዳዳዎቹ ውስጥ የሚያብለጨልጭ ነገር ይመለከታሉ።
 
ጥርጣሬ ያደረባቸው የፖሊስ አባላትም ምግቡን ዘርግፈው ሲፈተሹ፥ የሚያብለጨልጨው ነገር በ51 የማካሮኒ ፍሬዎች ውስጥ በአልሙኒየም ወረቀቶች የተጠቀለለ ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ አግኝተውታል።
 
ግለሰቡ ከዚህ በፊት በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በዚያው ፖሊስ መምሪያ ታስሮ እንደነበር የገለጸው ፖሊስ፤ ድርጊቱን የፈጸመው ጠያቂ ሰዎች የሚበዙበትን ሰዓት በማጥናት እና የፖሊስ አባላት ሊዘናጉ ይችላሉ ብሎ ባሰበበት ሰዓት መሆኑን ጠቅሷል።
 
ግለሰቡ በፈፀመው ወንጀል የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፓሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top