የዓድዋን ድል መንፈስ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ለውጥ እንደ ስንቅ መጠቀም ይገባል፡- የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ

6 Days Ago 222
የዓድዋን ድል መንፈስ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ለውጥ እንደ ስንቅ መጠቀም ይገባል፡- የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ
የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ነፃነት ትግል እንደ ችቦ መቀጣጠያ ሆኖ ማገልገሉን በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ተናገሩ፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትሯ እዚህ የቆምኩት የዓድዋ ድል በፈጠረው የነፃነት ጮራ ነው፤ እዚህ የቆምኩት በፓንአፍሪካኒዝም መስራች አባቶቻችን ትግል ምክንያት ነው ብለዋል።
 
የዓድዋ ድል መንፈስ በቀጣይ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ለውጥ እንደ ስንቅ መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።
 
አፍሪካ በቀድሞው መሪዎች ትግል ከቀኝ ግዛት መላቀቅ ብትችልም፤ ሕልሞቻቸውን እውን ለማድረግ ከውጭ ጥገኝነት በመላቀቅ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
 
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በብድር አቅርቦት፣ በብድር አመላለስ እና በሌሎች ዘርፎች የተጋረጠባትን አግላይና ኢፍትሃዊ አሰራሮችን ለማስወገድ፤ አፍሪካውያን ካዳያስፖራው ጋር በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
 
በዓለም ላይ ያለውን ኢፍትሃዊነትንና አግላይነትን ለመታገል ንግግርን ወደ ተግባር መቀየር በቁርጠኝነት መስራት ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
 
የዓለምን መፃኢ ጊዜ ካለ አፍሪካ ሰላም ማሰብ አይቻልም ብለው፤ ይህም በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ አፍሪካውያንንም ይመለከታል ነው ያሉት።
 
እኛ በካረቢያን ሀገራት የምንገኝ ዜጎች ከእናንተ አፍሪካውያን ጋር ከዘር ባሻገር ብዙ የሚያገናኙን ነገሮች አሉ፤ ይህን ማጠናከር እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
 
ይህ ዓለም ለህዝቦቿ እንዲሁም ለተፈጥሮዋ ትኩረት እንድትሰጥ፣ ወደ ቀልቧም እንድትመለስ መልዕክትን የሚያስተላልፍም ጭምር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሯ።
 
የታሪክን ጠባሶች ሽረን ወደ ተሻለችው ዓለም እንሻገር፤ ከኋላችን ያለፈው በድጋሚ ሊረብሸን አይገባም፤ ከዚህ በኋላ ለሚኖረን ጊዜ ከራሳችን ውጭ የሚያስቆመን መኖር የለበትም ብለዋል።
 
የህዝቦቻችንን መፃኢ እጣፋንታ የተሻለ ማድረግ ዛሬ በእኛ እጅ ነው፤ እኛም ዛሬ የዓድዋ ጀግኖችን ትግል ማድረግ፣ የነሱን ወጤት ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 
በላሉ ኢታላ

Feedback
Top