የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አንጎላ ልምዷን ለማጋራት ዝግጁ ነች ሲሉ ዛሬ ቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዧው ማኑኤል ጎሳዌስ ሎሬንሶ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ለአጀንዳ 2063 መሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው፤አፍሪካውያን በጋራ የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት መሥራት አለብን ብለዋል።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በመስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋጥ በሚደረገው ጥረት የአንጎላን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተገቢ ቦታ እንድታገኝ እንሚሠሩ ጠቅሰው፤ አፍሪካ በተመድ በቂ ውክልና እንድታገኝ በትብብር እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።
በቀጣይ አፍሪካውያን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰሩም አክለዋል።
ፕሬዚዳንት ዧው ማኑኤል ጎሳዌስ ሎሬንሶ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያን ሕዝብ አመስግነዋል።