ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የብረትና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጣሉ

10 Days Ago 263
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የብረትና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጣሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ብረታ ብረትና አልሙኒየም ምርቶች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እንዲጣል ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ተገለጸ።

የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች በውሳኔው ላይ ቅሬታ ቢያስነሱም ትራምፕ እቅዱ የአገር ውስጥ ምርቶችን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

በፈረንጆቹ መጋቢት 4 ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ የታሪፍ ጭማሪ ለሃገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደሚያስገኝም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡

"ይህ ትልቅ ነገር ነው፤ አሜሪካን እንደገና ሀብታም የማድረግ ጅማሬ ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።

"ሀገራችን የሚያስፈልጋት አሜሪካ ውስጥ የተመረተ ብረት እና አሉሚኒየም እንጂ ከውጭ የሚመጣ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።

በተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ይኖር ይሆን ተብለው ጥያቄ የቀረበላቸው ዶናልድ ትራምፕ፤ "ቀስ በቀስ ርካሽ መሆኑ አይቀርም" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

ውሳኔውን ተከትሎ ወደ አሜሪካ መሰል ምርቶችን የሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ አሜሪካ ከዓለም ቀዳሚዎቹ የብረታ ብረት አስገቢ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን ካናዳ፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ ደግሞ ዋነኛ አቅራቢዎች ናቸው።

ባለፈው ዓመት ካናዳ ከ50 በመቶ በላይ የሆነ አሉሚኒየም ለአሜሪካ ያቀረበች ሲሆን፤ የታሪፍ ውሳኔው በሥራ ላይ ከዋለ በካናዳ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሏል።

የካናዳ ፖለቲከኞች የትራምፕ ውሳኔ ሁኔታዎችን ይበልጥ ያወሳስባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በትናትናው እለት የካናዳው የኢኖቬሽን ሚኒስትር ፍራንኮ-ፊሊፕ ሻማፓኝ፤ የተጣለው ታሪፍ በፍፁም ምክንያታዊ አይደለም ሲሉ ተናገረዋል።

በሜሮን ንብረት

 


Feedback
Top