ዩክሬን ለጋሽ ሀገራቶቿ ከፊታቸው በተደቀነው ምርጫ እና በአካባቢያቸው ባለው የጂኦ ፖለቲካል ውጥረት የተነሣ የገንዘብ ድጋፍን ማረጋገጥ እየከበዳት መጥቷል ሲሉ የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሴርሂይ ማቼንኮ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ “እጅግ ብዙ መዳከም ይታየኛል። በወዳጆቻችን መካከል ድካም አለ። ጦርነቱን መርሳት ቢሹም ነገር ግን ጦርነቱ በሙሉ ጉልበት እየተካሄደ ነው” ሲሉ በሞሮኮ በማራኬሽ በተካሄደው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ስብሰባ ላይ በትላንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።
ዩክሬን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር ደጋፊዎችን ለማሳመን ሁለት እጥፍ ለመሥራት ተገድዳለች ሲሉ ሚኒስትሩ ተናገረዋል።
ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ5.4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል ተገብቶልናል ያሉት ሚኒስትሩ ይሁን እንጂ ከጃፓን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና በእርግጠኝነት ቁልፍ አጋራችን ከሆኑት ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት ቃልኪዳን እንጠብቃለን ሲሉ አክለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን የ52.6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ከመጪው 2024 እስከ 2027 (እ.አ.አ) ባሉት ጊዜያት ለመለገስ እየሠራ እንደሚገኝ ቪኦኤ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ ዩክሬን በመጭው አንድ ዓመት 18 ቢሊየን ዶላር እንዲሰጣት እንደምትጠብቅ ሚኒስሩ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በአውሮፓ ኅብረት በኩል የሩሲያ መንግሥት ንብረቶችን ለማገድ የተጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።