የትውልድ ባለአደራው - ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም

18 Hrs Ago 357
የትውልድ ባለአደራው - ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም

ለሀገራቸው ብዙ የለፉ፣ ብዙ የደከሙ ግን ብዙም ያልተነገረላቸው ናቸው። ከትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ ጣልያንኛ፣ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ አፋን ኦሮሞን በትንሹ መስማት እና መናገር ይችላሉ፤ ፈረንሳይኛ እና ዓረብኛም ይሞክራሉ።

መጽሐፍ አንባቢነታቸው፣ የተግባር ሰው መሆናቸው እና ሥራ ወዳድነታቸው የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸው እንዳስቻሉአቸው የሚያውቋቸው ይናገራሉ፤ በተለይም ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ዕውቀት “ተንቀሳቃሽ ቤተመጽሐፍት” አሰኝቷቸዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በወታደራዊ ሕይወታቸው፣ በመሪነታቸው እና በፖለቲከኛነታቸው ከፍተኛ ሚና በመወጣቸው ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የነገሥታቱ ቤተሰብ በመሆናቸው ደግሞ የኢትዮጵያ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክ ማኅደር ናቸው።

ራስ መንገሻ ሥዩም የተወለዱት ኅዳር 29 ቀን 1919 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው። ያደጉ ደንጎላት የተባለ የእንደርታ አካባቢ ሲሆን፣ አባታቸው ሥዩም መንገሻ ዮሐንስ የአፄ ዮሐንስ 4ኛ የልጅ ልጅ ናቸው። በጣሊያን ወረራ ወቅት ከአባታቸው ጋር ተማርከው በጣሊያን እስር ቤቶች ቆይተው ተመልሰዋል። ጣሊያን ከሀገር ከወጣች በኋላ እስከ ቀዳማይ ወያነ እንቅስቃሴ ድረስ ደጃዝማች ተብለው የተምቤን ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው ቆይተዋል።

በ1936 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ሊባኖስ ቤይሩት ተልከው ትምህርታቸውን በቤይሩት የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። ወደ እንግሊዝ ሀገርም በመጓዝ በሲቪል ምህንድስና ተመርቀዋል። ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በተለያዩ አካባቢዎች በኃላፊነት በመመደብ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎችን ሠርተዋል። በሚሾሙበቸው ግዛቶች ሁሉ አካባቢዎችን ከአካባቢዎች የሚያገናኙ ጎዳናዎችን፣ የከተማ ፕላንን እና የከተማ ውስጥ መሰረተ ልማቶችን በመሥራት ይታወቃሉ።

የጅባትና ሜጫ አውራጃ አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት የአምቦ ከተማ ፕላን እንዲኖራት፣ መንገድ እና መብራት እንድታገኝም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም አውራጃው ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን የሚያገናኙ መንገዶችን አሠርተዋል።

አስተዳዳሪ ተብለው በሚላኩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቁጭ ብለው በማዘዝ ሳይሆን ዝቅ ብለው በመሥራት እንዲሁም ያስተዳደሯቸውን አካባቢዎች በማቅናት የሚታወቁት ልዑሉ በጅባትና ሜጫ በቆዩባቸው ወቅቶችም ይህንኑ አስመስክረዋል።

የአርሲ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ሲሾሙ ደግሞ አርሲን ከባሌ ጠቅላይ ግዛት ጋር የሚያገናኛትን ትልቁ የገናሌ ወንዝ ድልድይ ሠርተዋል። የአካባቢው ሰዎች የተዳቀሉ ፀጉራም በጎችን እንዲያረቡ እና ለገበያ እንዲያቀርቡ፣ በባለቤታቸው ልዕልት አይዳ ደስታ አማካይነት የሴቶች የባልትና ልማት ማኅበር በኢንዱስትሪ ደረጃ ተቋቁሞ ከበጎቹ ፀጉር ምንጣፍና ሹራብ አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርብ በማድረግ የገበያ ትስስርን ፈጥረዋል። የሕዝቡን የውኃ ችግር ለመፍታት ከዓለም ባንክ ፈንድ በማፈላለግ የውኃ ጉድጓድ አስቆፍረዋል።

በ1946 ዓ.ም በወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት የሚባለው ገዥ ሆነው ሲሾሙ ውቢቷ ሐዋሳ አሁን ባለችበት ቦታ እንድትመሰረት ቦታውን በመምረጥ እና ፕላኗን በመሥራት የማይፋቅ አሻራቸውን አሳርፈውባታል። ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ ሀይቅ ላይ የተንሳፈፈችው እርሳቸው ከእንጨት ያሠሯት 12 ሰዎችን የምትይዝ ጀልባ ነበረች።

የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፕሮፔለር ሞተር ያላቸውን ዳሽ አውሮፕላኖችን ይዞ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል እንደማይችል ሲረዱ ለውጥ እንደሚያስፈልገው አመኑ። በወቅቱ የሥራና መገናኛ ሚኒስትር እና የአየር መንገዱ ቦርድ ሰብሳቢ ስለነበሩ አየር መንገዱ በገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆን ካስፈለገ የጄት ሞተር ያለውን ቦይንግ 720 ሊኖረው እንደሚገባው ለቦርዱ አቅርበው አፀደቁ።

የቦርዱን ውሳኔ ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ቢያቀርቡም ገንዘብ ስለሌለ አይቻልም ተባሉ፤ እርሳቸው ግን ተስፋ ሳይቆርጡ እቅዳቸውን ለጃንሆይ አቅርበው አሳመኑ። ንጉሡም ለአውሮፕላኖቹ ግዢ የሚያስፈልገውን 45 ሚሊዮን ዶላር ብድር ራሳቸው እንዲያፈላልጉ ውክልና ሰጧቸው። ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላም የአሜሪካ መንግሥት ብድሩን ፈቀደ፤ እርሳቸውም በደስታ ወደ ሥራ ገቡ። የአየር መንገዱን ባለሙያዎችም ለበረራ እና ለጥገና ወደ አሜሪካ ልከው በማሰልጠን አየር መንገዱን አጠናክረው ተወዳዳሪ አድርገውታል።

በሦስት ዓመታት እንዲጠናቀቅ የታቀደውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ሌት-ተቀን በመሥራት በአንድ ዓመት እንዲጠናቀቅ አድርገዋል። የዚህኑ የአፍሪካ አንድነት አዳራሽ ሥራ በሌሊት ሲያስተባብሩና ሲያሠሩ ንጉሡ አፄ ኃይለሥላሴ በድንገት በሌሊቱ የሥራውን ሂደት ለመከታተል አጃቢዎቻቸውን አስከትለው በቦታው ይደርሳሉ። ጃንሆይ ቀድሞውንም በትጋታቸውና በሥራ ወዳድነታቸው የሚያደንቋቸውን ራስ መንገሻን በይበልጥ በትጋታቸው እየተደነቁ ትከሻቸውን መታ መታ በማድረግ፤ ‘‘ራስ መንገሻ ትጋትህን እናደንቃለን፤ ሠራተኞችህም የዋዛ አይደሉም፤ እንደ ንቢቱ ታታሪ ናቸው፤ አፍሪካውያን እና ዓለም የሰጠንን ብርቱ አደራ በጊዜው አጠናቅቀን እንደምናሳያቸው ተስፋዬ ጽኑ ነው። በዚህ ሌሊት ብርዱ ሳይበግራችሁ የአንተም የሠራተኞችህም ብርታት እና ጥንካሬ በእውነቱ ይገርማል፣ ይደንቃል’’ በማለት እንዳደነቋቸው ይነገራል። ልዑሉም ጃንሆይን እጅ እየነሱ፣ ‘‘ጃንሆይ በእጅጉ የሚደንቀውስ የእርስዎ በዚህ ሌሊት በመካከላችን መገኘትዎ እንጂ… እኛማ ሥራችንም ነው፤ የእርስዎ የንጉሠ ነገሥታችን መንግሥት፣ አፍሪካውያን እና ዓለም አምኖ የሰጠን አደራ ነውና ኢትዮጵያችን በዓለም ፊት እንዳታፍር ነው እንዲህ ጠዋት ማታ ሳንል መትጋታችን፣ መሥራታችን…፤’’ ብለው መልሰውላቸዋል።

ባሕር ዳር ተለዋጭ የመንግሥት መቀመጫ እንድትሆን በማሰብ ባለሙያዎችን ከጀርመን በማስመጣት ፕላኗን አሠርተውላታል፤ እናም ዛሬ ያለችው ውቢቱ ባሕር ዳር የእርሳቸው ሀሳብ እና ተግባር ውጤት ነች።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መስመር 75ኛ ዓመቱን ሲያከብር በወቅቱ በፈረንሳዮች ብቻ ሲተዳደር የነበረውን የባቡር መስመር ከፈረንሳዮች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን አመራሮች እና ቴክኒሻኖችም በስፋት እንዲገቡበት አድርገዋል።

በጂቡቲ ወደብ ትጠቀም የነበረችው ኢትዮጵያ ትከፍለው የነበረው ቀረጥ ቀርቶ በነጻ እንድትጠቀም ከፈረንሳይ ጋር ተደራድረው አስፈጽመዋል።

ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ትውልድን በሚቀርጹ እና ለትውልድ በሚተላለፉ ሥራዎቻቸው ሁሌም ይወሳሉ። ከነዚህ የትውልድ ውርስ ከሆኑት የእርሳቸው ብቁ አመራር በየተመደቡባቸው አካባቢዎች እና በመላው ኢትዮጵያ ያሠሯቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው። እነዚህ ትምርት ቤቶች የበርካታ የሀገር ባለውለታዎች ማፍሪያ ሆነዋል።

በ1953 ዓ.ም አባታቸው ልዑል ሥዩም መንገሻ እነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በመሩት መፈንቅለ መንግሥት ሲገደሉ እርሳቸው አባታቸውን በመተካት የትግራይ ሀገረ ገዢ ሆነው ተመደቡ። በትግራይ ገዢነታቸው ወቅትም ቅድመ አያታቸው አፄ ዮሐንስ የመሰረቷትን መቐለ ፕላን ተሠርቶላት አሁን የያዘችውን ቅርፅ እንድትይዝ ያደረጉት እርሳቸው ናቸው።

በትግራይ አስተዳዳሪነታቸው ወቅት እጅግ በርካታ መንገዶችን እና ድልድዮችን ሠርተዋል፤ ከተሞች የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙም አድርገዋል። ሥራዎችን ሲሠሩም ሕዝቡን እያሳተፉ እና ራሳቸውም ወርደው በማሠራት ነው። እንደ ተራ ሠራተኛ የመንገድ ሥራ ላይ ቡልዶዘር እያሽከረክሩ፣ ከአለቶች ጋር እየታገሉ እውነተኛ የልማት አርበኝነታቸውን አስመስክረዋል።

ሕዝብን በለወጡ ሥራዎቻቸውም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። ከሁሉም ሽልማቶች የሚልቀው ግን በሕዝብ ልብ ውስጥ በፍቅር መንገሣቸው እንደሆነ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። በ2010 ዓ.ም መንግሥታዊ ኃላፈነትን በብቃት መወጣት በሚለው ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማትን አግኝተዋል።

ደርግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በሕዝብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ስለሚያውቅ እንደሌሎች ባለሥልጣናት አልያዛቸውም፤ ነገር ግን ዝም ሊላቸው እንዳልፈቀደ ሲያውቁ ወደ ሱዳን በመሰደድ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረትን (ኢዲኅ) መሥርተው ወደ ትግል ገቡ። የትጥቅ ትግሉ ብዙም አንደማያስኬድ ሲረዱ ወደ አሜሪካ አቅንተው ኑሮአቸውን በዚያ አደረጉ። ደርግ እንደወደቀም ግማሽ ጊዜአቸውን በኢትዮጵያ ግማሽ ጊዜያቸውን ደግሞ በአሜሪካ አድርገው ቀጠሉ።

በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ የሚኖሩት ልዑል ራስ መንገሻ “ረጅም ዕድሜ እና ጤና ለመታደል የተሰጠንን አደራ መወጣት እና ፈተናን በብቃት መወጣት አለብን” በማለት የራሳቸውን የሕይወት ልምድ ያካፍላሉ፤ "ለተግባረ ነፍስ ለተግባረ ሥጋ ለመብቃት፣ ወርቅ በእሳት እንደሚነጥር ሁሉ የሰውም ልጅ እንደ እሳት በሚያቃጥል የሕይወት ፈተና ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል። ይህን መሬት ጠብ የማይል ሀቅ፣ ከእኔ ግለ ሕይወት አንፃር ሳገናዝበው ረዥም ዕድሜና ጤና ከማታ እንጀራ ጋር መታደሌ፣ እንደ እሳት በሚነድ ሥቃይና መከራ ተፈትኜ ማለፌን ያስታውሰኛል" ይላሉ። "በ13 ዓመት ዕድሜዬ በንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ችሎት ተከስሼ በሞት እንድቀጣ ተደግሶልኝ የነበረው ፍርድ፣ እንደዚሁም የደርግን የመፈንቅለ መንግሥት አመፅ በትጥቅ ትግል ለመደምሰስ በበረሃና ሀገር ለሀገር በመንከራተት ያሳለፍኩት 17 ዓመት ከባድ የፈተና ዘመኖቼ ነበሩ፤" በማለት ነው ያሳለፉትን የውጣ ውረድ ሕይወት የሚያወሱት። ሕይወታቸውን የሚተርክ "የትውልድ አደራ" የሚል መጽሐፍ ለህትመት አቅርበዋል።

በለሚ ታደሰ


Feedback
Top