ኢ-ፓስፖርቱ ለዜጎች ጥራት እና ግልፅነት የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል፡- ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ

19 Hrs Ago 85
ኢ-ፓስፖርቱ ለዜጎች ጥራት እና ግልፅነት የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል፡- ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ
ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ የተመረተው እና ዛሬ ይፋ የተደረገው ኢ-ፓስፖርት ለዜጎች ጥራት እና ግልፅነት የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
 
አዲሱ ኢ-ፓስፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅት ፕሬዚደንት ታየ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች እና የጉዞ ሰነዶች ዘመኑን የዋጁ እና የተራቀቁ የደህንነት ባህሪያት እንዲኖራቸው መደረጉ ትልቅ እመርታ ነው።
 
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ተግባራዊ መደረጉ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር ለዜጎች የተሰጠውን ዋጋ የሚገልፅ ነው ብለዋል።
 
ፓስፖርቱ ማንኛውንም አይነት ማጭበርበር ለመግታት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
 
ዘመናዊ ሰነዶች የሰዎችን እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባሻገር ንግድን ለማሳለጥና ህጋዊ የስራ ዕድል ለማግኘት አስፈላጊ መሆናቸውንም አክለዋል።
 
ኢ-ፖስፖርቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በቶፓን ሴኪዩሪቲ ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር አማካኝነት በሀገር ውስጥ መመረቱ በመድረኩ ላይ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ፣የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

Feedback
Top