Search

ባለውለታዎችን እያከበረ ነገን የሚገነባው የመደመር ጉዞ

ሓሙስ ኅዳር 10, 2019 189

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቦሌ 57 ሄክታር የኮሪደር ልማት ክልል፣ በዐደይ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ እግር ኳስ አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የተሠራውን መታሰቢያ ሐውልት በይፋ መርቀዋል።

ይህ ክንውን የአንድን ታላቅ ሰው ገድል ከማስታወስ ባለፈ፣ በዘመናዊው የከተማ ልማት ውስጥ ታሪክን የማስቀጠል ራዕይን የሚያንጸባርቅ ነው።

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በተጫዋችነታቸው ለብሔራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ በ1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያነሳ ማድረግ የቻሉ ብቃት ያላቸው አሠልጣኝ ነበሩ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን በከፍተኛ አመራርነት በቆራጥነት በማገልገላቸው "የጅብራልተሩ ዐለት" የሚል ስያሜ አትርፈዋል፡፡ በፊፋ ሥራ አስፈጻሚ አባልነታቸውም የአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች እንድትታገድ እና የአፍሪካ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ኮታ እንዲያድግ በመታገል ከዘረኝነት የፀዳ እግር ኳስ እንዲኖር የማይረሳ ዐሻራ አሳርፈዋል። የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የስፖርት ኮሜንታተር መሆናቸውም የስፖርት ታሪካችንን ይበልጥ ያደምቀዋል።

በመደመር እሳቤ ዐርበኝነት ትላንትን ከዛሬ በማስተሳሰር ቀደምት ትውልዶች ያስመዘገቧቸውን ድሎች እና ውርሶች ጠብቆ ማስፋትን እና ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስተላለፍን ያካትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት እንዳስገነዘቡት ለኢትዮጵያ ውለታ የዋሉ ዐርበኞችን እና ታላላቅ ሰዎችን ምልክት በአደባባይ ማቆም መጪው ትውልድ እነሱን እያየ እንዲነቃቃ፣ አቅሙን እንዲያሳድግ እና የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ እንዲያስጠራ የሚያነሳሳ የአደራ ጥሪ ነው።

ይህ የትውልድ ቅብብሎሽ መንፈስ በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና የከተማ ማደስ ሂደት ውስጥ በተግባር እየተንጸባረቀ ይገኛል። በዑራኤል ስፖርት ፓርክ በሕይወት ያሉ ስድስት እንስት የኦሊምፒክ ጀግኖችን ጨምሮ ለ15 የአትሌቲክስ ፈርጦች ሐውልት መቆሙ ባለውለታዎችን በሕይወት እያሉ የማክበር መልካም ልማድን አጠናክሯል።

በተመሳሳይም በዐርበኞች የድል በዓል ወቅት ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ለስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ለጥላሁን ገሠሠ፣ ለማሕሙድ አሕመድ፣ ለዓሊ ቢራ እና ለሃጫሉ ሁንዴሳ በመዲናዋ መታሰቢያ መቆሙ ጥበብ እና ባህል የማኅበራዊ ሕይወትና የታሪክ ትዝታ አካል መሆናቸውን ያሳያል።

በፒያሳ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያም የቀደምት አባቶች እና እናቶችን የነፃነት ገድል ከዛሬው የልማት እንቅስቃሴ ጋር በማገናኘት የጋራ ታሪካዊ ማዕከል ሆኗል።

የቦሌ 57 ሄክታር ኮሪደር 34 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 8 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መስመር፣ 150 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያዎች፣ ቤተ መጻሕፍት እና የስፖርት ሜዳዎችን አካትቶ መገንባቱ ምቹና ሰው ተኮር የከተማ ምህዳር ፈጥሯል።

ነዋሪዎች በንጹሕና ምቹ ከባቢ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የቀደምት ጀግኖችን ሐውልት መመልከታቸው የትጋትና የመስዋዕትነትን ዋጋ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እንዲገነዘቡ ያደርጋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ከተማ የምትገነባው በመንገድ እና በሕንፃ ብቻ ሳይሆን ታሪኳን የሠሩ እና ለኢትዮጵያ ውለታ የዋሉ ባለውለታዎቿን በክብር በማስቀጠልም ጭምር ነው።

የአፍሪካ እግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን መዘከር ታሪክን ከዛሬ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለነገው ትውልድ ኩራትና መነሳሳት እንደሚፈጥር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ልማት የዛሬን ከተማ ብቻ ሳይሆን የነገንም ታሪክ ስለሚጽፍ፣ ታሪክን እያከበሩ፣ ማንነትን እያጠናከሩ እና ዐሻራን ለትውልድ እያስተላለፉ መቀጠል የዘመናዊ ከተማ ግንባታ ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ይቀጥላል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: