Search

የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን የታላቅነት ማሳያ እያደረጋት ነው፡- የአህጉራዊ ጉባኤው ተሳታፊዎች

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 120

የመደመር እሳቤ አዲስ አበባን የአፍሪካ እውነተኛ መዲና እና ኢትዮጵያን ደግሞ የታላቅነት ማሳያ እያደረጋት መሆኑን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመደመር መንግሥት እሳቤ ከተሞቿን በቴክኖሎጂ ለማዘመን፣ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እና የተቀላጠፈ አኗኗርን ለመፍጠር የሠራቻቸው ሰፊ ሥራዎች ፍሬ እያፈሩ ይገኛሉ።

ይህንኑ እውነታ በሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተሳታፊዎች በሰጡት ምስክርነት አረጋግጠዋል።

ተሳታፊዎቹ በአዲስ አበባ ባደረጉት ምልከታ ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትክክል የአፍሪካ መዲና እየሆነች መምጣቷን በመግለጽ፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታላይዜሽን የታየውን ለውጥ አድንቀዋል።

የአዲስ አበባ ንጽህና፣ መሠረተ ልማት፣ የህዝቧ መስተንግዶ እና አገልግሎት አሰጣጥ እንዳስገርሟቸው ገልጸው፣ ከተማዋ ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ከተሞች ጋር እንኳን የምትስተካከልና ከጎረቤት ከተሞች በተሻለ የቴክኖሎጂ እድገትና ውበት የተጎናጸፈች መሆኗን መስክረዋል።

የመደመር እሳቤ የሀገር ውስጥ አቅምን አስተባብሮ ጥቅም ላይ በማዋል የተሻለች ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል ልዩ እሳቤ መሆኑን ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፣ እሳቤው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊተገበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፓርቲዎች በጋራ መሥራትና ራዕይ መከተል አስፈላጊነትን የጠቀሱት ተሳታፊዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ የመደመርን እሳቤ በተግባር ያሳየበት መንገድና የመሥሪያ ቤቱ አደረጃጀት እጅግ ማራኪ መሆኑን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ በመሶብ እና በሌሎች የመረጃ ማዕከላትና ሙዚየሞች ባደረጉት ጉብኝት፣ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን እያደረገች ያለው ጉዞ ከዓለም ጋር እኩል እንድትራመድ አቅም የፈጠረላት መሆኑን አመላክተዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠንና የአፍሪካን የጋራ ልማት ለመቀረጽ የሚያስችል መድረክ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው የለውጥ ጉዞ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የራስን አቅም በማስተባበር ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል ትልቅ የተግባር ማሳያ ሆኗል።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: