Search

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ታሪካዊ ግንኙነታቸውንና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 215

የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል፣ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጃሲንቶ ማሲንጋ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት፣ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ጠንካራና በውጤት የታጀበ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣና የመረጋጋት ምሰሶ መሆኗን በመግለጽ፣ ሁለቱ ሀገራት በቀጣናው መረጋጋት ላይ በቅርበት መሥራታቸው ዘርፈ-ብዙ ውጤት ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

በቅርብ ጊዜያት የሁለቱ ሀገራትን ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ የስምምነት ማዕቀፍ መፈረም የአሜሪካ አምባሳደር እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለተጫወቱት የጎላ ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሕዝቧን አሁናዊ እና ቀጣይ ፍላጎት ለመመለስ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምትጥር ሀገር መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ አሜሪካም በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተውን የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂክ አጋርነት መሠረት እያደረገች ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

አምባሳደር ኤርቪን ጃሲንቶ ማሲንጋ በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜና ከሁኔታዎች የተሻገረ መሆኑን ገልጸው፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥታ እንደምትሠራ አረጋግጠዋል።

አሜሪካ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመከላከል እና በወታደራዊ ዘርፍ የተጀመሩ ስትራቴጂያዊ ትብብሮችን አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ በላከልን መረጃ አመላክቷል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: