የኢትዮጵያ ታሪክ የሚነበበው በተናጠል በቆሙ ድምፆች ሳይሆን በብዙኃን ዜማዎች ውህደት ነው።
ሕዝቦች በብሔር፣ በሃይማኖት እና በአመለካከት ልዩነት ሳይታጠሩ ልባቸውን ለአንድ ዓላማ ባዋሃዱባቸው ዘመናት ሁሉ የማይደፈር የሚመስለውን ገደል ተሻግረው ተአምራዊ ድሎችን ተጎናጽፈዋል።
የዓድዋ ታሪካዊ ድል የዚህ ሕያው ማሳያ ነው። የውጭ ወራሪ ኃይል በመሪዎች እና በአካባቢዎች መካከል ልዩነትን በማስፋት ከውስጥ ሊበትነን ቢሞክርም፣ መሪዎች እና ሕዝቡ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በመዝመታቸው ቅኝ ገዥውን ኃይል በመደምሰስ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ፋና ለኩሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ከስምንት አስርተ ዓመታት በኋላም በካራማራ ተራሮች ላይ የውስጥ እና የውጭ ውጥረት ሳይበግራቸው የሉዓላዊነት አንድነታቸውን ያስከበሩት በጋራ ዓላማ በኅበረት በመሰለፋቸው ነው።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የዓለም አቀፍ ተቋማት የብድር በር ሲዘጋባቸው በራሳቸው ላብ እና ጥሪት ሰባ አራት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የሚይዘውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገንብተው ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈዋል። በዚህም በኅብር ሲቆሙ የማይችሉት ነገር እንደሌለ ለዓለም አረጋግጠዋል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ኅብረቷን ባላጠናከረችባቸው እና የውስጥ መከፋፈል በነገሠባቸው ዘመናት የከፈለችው ዋጋ መራራ ነበር። ከ70 ዓመታት በዘለቀው ዘመነ መሳፍንት የመሳፍንት ሽኩቻ ማዕከላዊ አቅሟን አሽመድምዶ፣ ኢኮኖሚዋን አድቅቆ እና ከዓለም አቀፍ መድረክ አግልሏት ቆይቷል። ያ ዘመን ዓለም የኢንዱስትሪ አብዮቶች ሲያቀጣጥል ኢትዮጵያ ግን በምዕተ ዓመት ወደኋላ እንድትቀር ያደረገ ትልቅ ታሪካዊ ስብራት የገጠመበት ወቅት ነበረ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይም የእርስ በርስ ግጭቶች እና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ከድርቅ ጋር ተዳምረው የድህነት ምሳሌ እስከመሆን የደረሰ ጥልቅ ተግዳሮት ውስጥ ከትተዋት ነበር። ታሪክ በግልጽ እንደሚያስተምረን ኢትዮጵያን የሚፈትናት የውጭ ጠላት ብርታት ሳይሆን የውስጥ መነጣጠል ድካም ነው።
ይህንን የዘመናት ስብራት ለመጠገን እና ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ጸጥታ እና ብልጽግና ለማሻገር የመደመር መንግሥት ሰፊ የሪፎርምና የግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የመደመር ፍልስፍና የብቸኝነት ጉድለትን በኅብር በመሙላት ላይ የተመሠረተ ነው። የሰው ልጅ የሕይወት፣ የደኅንነት፣ የነጻነት እና የክብር ፍላጎቶች ተደማሪ ባሕርይ ስላላቸው፣ ብቻዬን ማሳካት እችላለሁ የሚል መነጣጠል ወደ ውድቀት ይመራል።
ስለሆነም ብዝኃነትን ከሚጨፈልቀው የፍጹም አንድነት ጽንፈኝነትም ሆነ የጋራ ትስስርን ከሚንደው የፍጹም ልዩነት ትርክት በመውጣት፣ ብዙ ሆነን አንድ፣ አንድ ሆነንም ብዙ የሚያደርገውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት የመደመር ዋነኛ ዕይታ ነው።
እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚጸናውም ይህንኑ የብቸኝነት ጉድለት በመደመር በመሙላት ነው። ፌዴራሊዝም የመገለል እና የመነጠል አጥር ሳይሆን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግሥታዊ መብትን ከጋራ ጥቅምና ወንድማማችነት ጋር የሚያስተሳስር ድልድይ ነው።
ይህንን እሳቤ በተቋማዊ መሠረት ላይ ለማኖርም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰፊ አሳታፊ ሥራዎችን አከናውኗል። ከሰፊው የሕዝብ ውይይት የተገኙ አጀንዳዎች ተጣርተው ዋና ዋና ምሰሶዎች በመለየት እና ተወካዮችን በማወያየት የተዘጋጁ ምክረ ሀሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልሎች ማስረከቡ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ቀሪ የጸጥታ እና የፖለቲካ ልዩነቶችንም በዚሁ የምክክር እና የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ ውስጥ በመፍታት የተጀመረውን የሰላም ጉዞ ፍጹም የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ዘንድሮ ኅዳር 29 ቀን 2019 ዓ.ም በውቢቷ ጅማ ከተማ የሚከበረው 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንም የዚሁ የመደመር መርሕ ሕያው ማሳያ ነው።
በብዝኃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው ይህ በዓል፣ ከባህላዊ ትርዒት ባለፈ የወንድማማችነት፣ የአብሮነት እና የምክክር ቀናትን በማካተት ለቀጣይ ትውልድ ሰላም ፍኖተ ካርታ መሠረት የሚጥል የጋራ ቃል ኪዳን መድረክ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ ኅብሯን ጌጥ አድርጋ መሥራት ምርጫ ሳይሆን አማራጭ የሌለው የሕልውና እና የብልጽግና መንገድ ነው። ልዩነቶቻችንን ወደ ውበት እና ፈጠራ፣ ቅራኔዎቻችንን ወደ ምክክር እና መግባባት፣ አቅማችንን ደግሞ ወደ ጋራ ልማት በመቀየር፣ የትናንቱን ታሪካዊ ድል በዛሬው የሥልጣኔ ጉዞ ላይ ደግመን መሥራት የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: