በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ባለ አደራ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳሞራ ያህያ የባለአደራ አስተዳደሩ ዋና ዓላማ ዕርቅ እና ሰላም በማስፈን ሕዝቡን ወደ ተረጋጋ ሕይወት መመለስ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትላልቅ ውጤቶች እንደተመዘገቡ እና በተለይም በጸጥታ እጦት ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የትግራይ ከተሞች ወጣቶች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባቸው መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ይህንን ትልቅ ውጤት ጠብቆ በቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሕዝባዊ ፖሊሶች ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው በሰላም ግንባታ ላይ እየተጫወቱት ያለው ሚና ሊመሰገን የሚገባው መሆኑንም ተናግረዋል።
ወደ ከተሞች ተሰድዶ የነበረው የትግራይ ወጣት ወደ ቀየው መመለስ መጀመሩ ለሰላም የተከፈለው ዋጋ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፣ የትምህርት ቤቶች መደበኛ የማስተማር ሂደት መጀመራቸውም የሚመሰገን መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ከተሞች የሚታዩትን የስርቆት እና ሌሎች ወንጀሎችን ማኅበረሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሊታገላቸው እንደሚገባ አመላክተዋል።
ሕዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን ሲጠብቅ ሰላም ማስፈን ላይ የሚኖረውን ጥቅም የአዲግራት ከተማ ሕዝብ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን እና ሁሉም ሊከተለው የሚገባው መንገድ እንደሆነም ገልጸዋል።
በነዳጅ አቅርቦት ላይ የነበረውን ችግር ለመፍታት በፌዴራል መንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳሞራ ያህያ፤ ባለአደራ አስተዳደሩ ሕገወጥ የነዳጅ ንግድን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ሁሉም አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: