ባለፉት ሥድስት ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባ እና ዕድሳት አገልግሎት በኦንላይን ተሰጥቷል፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

7 Days Ago 263
ባለፉት ሥድስት ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባ እና ዕድሳት አገልግሎት በኦንላይን ተሰጥቷል፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
ባለፉት ሥድስት ወራት የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን በተከናወነው ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባ እና ዕድሳት አገልግሎት በኦንላይን መሰጠቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
 
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች የጋራ ጉባዔ''በጥራት ወደ ተሳለጠ የንግድ ሥርዓት'' በሚል መሪ ቃል በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
 
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና ገበያውን ለማረጋጋት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ማዕከላትን ወደ 1 ሺህ 213 በማድረስ ምርት ለማቅረብ ተሰርቷል።
 
በሕገወጥ ንግድ ላይ በተሳተፉ ከ100 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ እና የተለያየ ደረጃ ቅጣት የተላለፈ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ በ1 ሺህ 16 በሚሆኑት ላይ ደግሞ እስራት እና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።
 
በነዳጅ ስርጭት እና ግብይት ላይ በተደረገ ቁጥጥር 325 ሺህ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር በማዋል በሂደቱ የተሳተፉ ኩባንያዎች 116 ሚሊዮን ብር እንዲቀጡ መደረጉንም ጠቁመዋል።
 
በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ኤሌክትሪክ ዘርፍ በተከናወነው የውጭ ንግድ ባለፋት ስድስት ወራት ከ3 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።
 
በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፌደራል እና የክልል የንግድ ዘርፍ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
 
በአስረሳው ወገሼ

Feedback
Top