የእድገት ምልክት፣ የአፍሪካ የልብ ምት እና የአንድነት መቀመጫ:- አዲስ አበባ

13 Days Ago 372
የእድገት ምልክት፣ የአፍሪካ የልብ ምት እና የአንድነት መቀመጫ:- አዲስ አበባ

አዲስ አበባ ለፈተናዎች አልበገርም ብላ የለውጥ እና የሽግግር ምልክት ሆናለች ይላሉ የደቡብ አፍሪካው ብሔራዊ የትምህርት አገልግሎት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ቡሳኒ ንካዌኒ። 

በደቡብ አፍሪካው ጋዜጣ እና የበይነ መረብ ዜናዎች አሰራጭ ዴይሊ ማቭሪክ ላይ የመዲናዋን ለውጥ በማድነቅ በከተቡት የግል አስተያየት አዲስ አበባ ለውጥ እንዳዘገመባቸው ወይም ባሉበት እንደቆሙት እንደ ደርባን፣ ሉዋንዳ፣ ኪንሻሳ እና ሞምባሳ ከተሞች አይደለችም ይላሉ።

ተራራማ ከተማ ሲሉ የገለጿት አዲስ አበባን የተስፋ ተቀርኖዎችን እምቢኝ በማለት የራሷን ማንነት በራሷ መንገድ እየቀረጸች መሆኗን ይገልጻሉ።

ተስፋ መቁረጥ ልክ እንደ በረ ቀልጦ ከተማዋ ወደ ታላቅነት የመቀየር ጉዞ ላይ እንደምትገኝም አመላክተዋል።

አዲስ አበባ ታሪኳን እና የአፍሪካ ብርሃን የመሆን ሕልሟን አስታርቃ በሰሜናዊ እና ደቡባዊ የዓለም ንፍቀ ክበቦች ውስጥ ካሉ ጉምቱ ከተሞች የስሪት ሰንሰለት ሰብራ ራሷን ነጻ አውጥታለች።

ቡሳኒ ንካዌኒ አዲስ አበባ ሁሌም የብርሃን ምንጭ ናት ይላሉ። አዲስ አበባ ከተቆረቆረችበት እ.አ.አ በ1886 ዘመን እስከ አሁን የነጻነት እና አንድነት ምልክት ሆና ቀጥላለች በማለትም ገልጸዋታል።

በሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎቿ መዲናዋ የራሷን ትርክት እየቀረጸች ነው ያሉት ፀሐፊው አዲስ አበባ ልዩ ያደርጋታል ያሉትን ሀሳብ በዚህ መልኩ ያስቀምጣሉ።

“አዲስ አበባ ልክ እንደ ካይሮ የስማርት ከተሞች ልማት ሰው ሰራሽነት ማንነቷን ያነጠፈባት ወይም ልክ እንደ ኬፕ ታውን ሀብታሞች ድህነት ያለበትን ከተማ እንደቀየሩትና የከበርቴዎች እንክብካቤ የሚደረግላት ከተማ አይደለችም፤ ይልቁንም ድፍረት የተሞላበትን እሳቤ በመተግበር ቀስ በቀስ ግርማ ሞገሷንና ውበቷን እየገለጠች ያለች ከተማ ናት” ሲሉ ይገልጻሉ።

የአዲስ አበባ ለውጥ ተጨባጭ ነው አሮጌ ሕንጻዎች በግዙፍ ሕንጻዎች መተካት ጀምረዋል፤ የመሰረተ ልማቱ ግንባታ፣ ከተማዋን የማስተሳሰር ስራ እና የትራንስፖርት አገልግሎቱ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን መስክረዋል።

ማራኪ የእግረኛ መንገዶች፣ የአደባባዮች ውበት፣ የትራፊክ መብራቶች እና ሌሎች የሚታዩ ለውጦች አዲስ አበባ የለውጥ ድባብ እንድትፈጥር ማድረጉን ይናገራሉ።

በከተማዋ ያሉ አስገራሚ ለውጦች በየቦታው ቆም ብለህ አየር እየወሰድክ ነገሮችን በጥሞና ለመመልከት ይጋብዛል ሲሉም አክለዋል።

ቡሳኒ ንካዌኒ በአዲስ አበባ ለውጥ የተደመሙበትን የግል ምልከታ ማንሳታቸውን በመቀጠል አዲስ አበባ የተለወጠችው በመሰረተ ልማቷ እና በኢንዱስትሪ ልማቷ ብቻ አይደለም በሕዝቧ ጭምር እንጂ በማለት ከትበዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች ልባቸውን በኩራት ሞልተው በእነዚህ መንገዶች ላይ ይንቀሳቀሳሉ። ውበትን ያየሁት የከተማው መሰረተ ልማቶች ላይ ብቻ አይደለም ሕዝቡ ላይም እንጂ ይላሉ።

ነዋሪዎቹ የከተማዋ የለውጥ መንፈስ ተጋብቶባቸዋል። በተንቀሳቀስኩባቸው ቦታዎች የሕዝቡ ውበት፣ መስተጋብር፣ ባህል እና ሰው አክባሪነት እውነትም አዲስ አበባ ምድረ ቀደምት ናት እንድል አስገድዶኛል በማለትም ይገልጻሉ።  

ነዋሪዎቿ መንፈሳዊ እና ውስጣዊ ውበታቸው ማራኪ ነው ይላሉ በአስተያየታቸው። ለንካዌኒ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ አይደለችም የብዙ ነገር ምልክት ናት። የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ማዕከል ጭምር እንጂ።

ማዕከላዊቷ አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎች የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመመስረት አንስቶ እስከ አሁን በርካታ ቁልፍ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ይሰበሰቡባታል።

እንደ ኒካዌኒ ገለጻ አዲስ አበባ የፓን አፍሪካኒዝም ሀሳብ ተጸንሶ የተወለደባት ከተማ መሆኗ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ቀጣናዊ ፍላጎቶችና ፉክክሮች፣ ብሔራዊ ጥቅሞች እና የሀሳብ ተቃርኖዎች ያላቸውን አካላት በሙሉ አቅፋ ይዛለች። ይህም የባለ ብዝሃ ወገን ዲፕሎማሲ መናህሪያ እና ምልክት ያደርጋታል በማለትም ገልጸዋታል።

ከሁሉም የዓለም ክፍሎች ዲፕሎማቶች አዲስ አበባ ይከትማሉ፤ ሰላም፣ ኒዎ ኮሎኒያሊዝም፣ ጸረ-ኢምፔሪያሊዝም፣ ልማት እና ሌሎች ግዙፍ አጀንዳዎችን በሻንጣቸው ይዘው መጥተው ይነጋገሩባታል።

አጀንዳ 2063 የአፍሪካ እና ቀጣናዊ ትብብርን ማሳኪያ የጋራ ቃልኪዳን ሰነድ ነው። የአፍሪካውያንን እድገት እና ብልጽግና ሕልም በውስጡ አቅፎ ይዟል። ይሄ አጀንዳ በየጊዜው በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ ቃል ኪዳን ይታደስባታል።

አዲስ አበባ ከመሰብሰቢያነት ባለፈ የአንድነት ማቀጣጠያ ስፍራ፤ የአፍሪካ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕልሞች መልክ የሚይዝባት እምብርት ነች ሲሉም ንካዌኒ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ።

አዲስ አበባ ስሟ እንደሚናገረው አዲስ ናት ሁሌ እንደአዲስ የምትፈካ አበባ ናት፤ ደማቅ ውበቷ ዘመናት የማይገድቡት እና የማይለውጡትም ጭምር።

የአፍሪካ ታሪክ ተናጋሪ የሆነችው አዲስ አበባ አበቦቿ ደርቀውም ሆነ ረግፈው አያውቁም ሁሌም እንደ አዲስ ይታደሳሉ ሲሉ ጥንካሬዋን ያነሳሉ።

አዲስ አበባ ለበርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳትበገር በማንነቷ ቀጥላለች ያሉት ንኮዌኒ መዲናዋ ትናንቷን ሳትረሳ ከዘመናዊነት ጋር ተጣምራ ጉዞዋን ቀጥላለች ብለዋል።

በአዲስ አበባ የወጣው ፀሐይ የመዲናዋን መንገዶች ብቻ የሚያፈካ ሳይሆን ለመላ አፍሪካ መጻኢ ጊዜ ብሩህ መሆንን የሚያበስር ጭምር እንጂ ይላሉ።

አዲስ አበባ፤ አስገራሚ የመንገድ መብራቶቿ፣ በየጊዜው እየፈኩ ያሉት ዛፎች፣ ጨዋ ሕዝቦቿ እና እያደጉ የመጡት ሕልሞቿ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሕልም ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላት የሚል እምነት ዳግም እንዲጣልባት አድርጓል ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ለውጧ የሚያሳምን፣ አቅምን የሚፈትሽ እና ራስህን እንድትለውጥ የሚያደርግ ማለታቸውን ዴይሊ ማቭሪክስን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

ከተማዋ በብዝሃ እድገት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት፤ አዲስ አበባ የሆነችው በስሟ ብቻ ሳይሆን በአዲስ መንፈሷም ጭምር ነው በማለትም አድናቆታቸውን ችረዋታል።

አዲስ አበባ ለውጥን አርግዛ አዲስ ማንነቷን ልትወልድ ተቃርባለች የሚሉት ጸሀፊው፤ የከተማዋ ውበት ያረፈው በአይበገሬነቷ እና በያዘችው ተስፋ ላይ ነውም ይላሉ።

ቡሳኒ ንካዌኒ በዴይሊ ማቭሪክ ላይ የአዲስ አበባን ለውጥ አስመልክተው ያሰፈሩትን  ጽሁፍ  በድንቅ አገላለጽ ይቋጩታል።

“አዲስ አበባ አንቺ ሁሌም የአፍሪካ ከተማ ልብ ሆነሽ ትቀጥያለሽ፣ ሕያዊቷ አዲስ አበባ እንዳለቅስ አታድርጊኝ፣ አዲሱ የዘመናዊነት የፍቅር ጊዜያችን ሁሌም ጸንቶ ይቀጥላል”  

ዘመናዊነት እና አይበገሬነት የተስማሙባት እና የተጋመዱባት የአፍሪካ የልብ ምት የሆነችው ከተማ፤ አዲስ አበባ በማለትም ጭምር።


Feedback
Top