ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 8 ሺህ 524 ተማሪዎችን አስመረቀ

5 Mons Ago 795
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 8 ሺህ 524 ተማሪዎችን አስመረቀ

አንጋፋው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 8 ሺህ 524 ተማሪዎች አስመርቋል። 

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በክረምት፣ በተከታታይና በርቀት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችን በሰርትፍኬት፣ በመጀመሪያ እና በማስተርስ እንዲሁም በዶክትሬት ደረጃ ነው ያስመረቀው፡፡

በዕለቱ ከተመረቁ 8 ሺህ 524 ተማሪዎች ውስጥ 3 ሺህ 34 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

በመርሃግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር መንገሻ አየነ፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 60 አመታት ለሀገር ብሎም ለዓለም ምሁራንን ያበረከተ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት፣ ማህበረሠብ ተኮር ስራዎችና አለም አቀፋዊነትን አልሞ እየሠራ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ፤ የአየር ንብረት ለውጥን በዕውቀት እና በተግባራዊ አረንጓዴ ልማት ላይ በማተኮር እተየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በስራ ፈጠራና ቅጥር ብቁ ምሩቃንን እያፈራ መቀጠሉን በማስገንዘብ ለምሩቃኑ መልካም ዕድል ተመኝተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት ካስመረቃቸው መካከል በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 58 ስፔሻሊስቲ እና 4 ሰብ ስፔሻሊስቲ ሃኪሞች እንዲሁም በህክምና አመራርነትም 6 የሰርትፍኬት ምሩቃን ይገኙበታል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ተመራቂ ተማሪዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የተመራቂ ወላጆች ተገኝተዋል፡፡

በራሄል ፍሬው


Feedback
Top