በናይጄሪያ የትምህርት ቤት ሕንጻ ተደርምሶ 22 ሕጻናት ህይወታቸው አለፈ

6 Mons Ago 662
በናይጄሪያ የትምህርት ቤት ሕንጻ ተደርምሶ 22 ሕጻናት ህይወታቸው አለፈ

በናይጄሪያ አንድ የትምህርት ቤት ሕንጻ ላይ በደረሰ የመደርመስ አደጋ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሆኑ 22 ሕጻናት ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል፡፡   

የሃገሪቱ የማዕከላዊ ክፍል በሆነውና ፕሌቱ በተባለ ግዛት ውስጥ በሚገኝው ትምህርት ቤት ላይ በደረሰው አደጋ ከ130 በላይ ህጻናት ጉዳት እንደደረሰባቸውም የግዛቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በግዛቲቱ ዋና ከተማ ጆስ ውስጥ የሚገኘው እና ሴይንት አካዳሚ በተባለው ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች በፈተና ላይ ሳሉ ሕንጻው እንደተደረመሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኛው ህጻናትም 15 እና ከዚያ በታች መሆናቸው ተጠቅሷል።

አደጋው የደረሰበት ትምህርት ቤት ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች ይገኙበት እንደነበርም ነው የተገለጸው።

ለትምህርት ቤቱ ሕንጻ መደርመስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ አደጋው የተከሰተው በግዛቲቱ ውስጥ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከባድ ዝናብ ከጣለ በኋላ ነው ተብሏል።

በናይጄሪያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ አደገኛ የሕንጻ መደርመሶች ያጋጠሙ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2021 በሌጎስ ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትልቅ ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ 45 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።


Feedback
Top