ውዷ ሐብታችን መሬት

7 Mons Ago 1109
ውዷ ሐብታችን መሬት

የሰው ልጅ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ አረንጓዴያማ የምድራችን ቦታዎችን ወደ በረሃማነት በመቀየር ከፍተኛ መዘዝ በምድር ላይ እያስከተለ ነው።

የዓለም ሙቀት መጨመር እና የሰው ልጅ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ ፕላኔታችን መሬት በቃኝ ብላ ምቹ ያልሆነውን ማንነቷን እንድታሳይም አድርጓታል።

እናም ይህ ሁኔታ እየበረታ በመሄዱ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም የመሬት ገፅታ ወደ በረሃማነት ተቀይሯል።

በአውሮፓውያኑ 2019 በወጣ መረጃ በዓለም ላይ የመሬት መራቆት ተከስቷል፤ በታሪክም የደን ሽፋን መጠን ከ30 እስከ 35 በመቶ መራቆቷ ይነገራል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ይህ መራቆት በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰተም ነው ።

እየከተሜነት መስፋፋት፣ የማዕድን ማውጣት ስራ፣ እርሻ እና የእንስሳት እርባታ ተጠቃሾች ናቸው።

በነዚህ ተግባራት ውስጥ ዛፎች እና ሌሎች ዕፅዋት ይወድማሉ ለሰብሎች ጠቃሚ የሆነው በአፈር ውስጥ ያለ ንጥረ ነገር እንዲሟጠጥ ይሆናል።

በዚህ ሳቢያ የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ነው በፕላኔታችን የድርቅ አደጋ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው።

በአውሮፓውያኑ 2030 ወደ 50 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ሊያፈናቅሉ በሚችሉና ለበረሃማነት ተጋላጭ በሆኑ ደረቅ ቦታዎች ላይ ወደ 2 ቢሊዮን የሚጠጉ የዓለማችን ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።

የበረሃማነት አደጋው ድሆችንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን በከባድ ሁኔታ ይመታል። ምክንያቱ ደግሞ በተጎዱ አካባቢዎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የእርሻ ስራ የተለመደ በመሆኑ ነው።

እንደ የአውሮፓ ኮሚሽኑ የዓለም በረሃማነት አትላስ ጥናት መሠረት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የምድር ይዞታ የተራቆተ ሲሆን፤ በ2050 ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የመሬት ክፍል ሊራቆት ይችላል ሲል ገልጿል።

አፍሪካ እና እስያ ደግሞ በዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው።

ታድያ ይህንን በረሀማነትን ለመከላከልና ለዓለም ህዝብ ስለችግሩ ግንዛቤ ለመፍጠር በየዓመቱ ሰኔ 10 በረሃማነትን እና ድርቅን የመዋጋት የዓለም አቀፍ ቀን ተደርጎ ይከበራል።

ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት መንግስታት፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በጋራ በመሆን አካባቢን ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት እና የመሬት ሐብቶችን በብቃት ለማስተዳደር አንድ ያደርጋል ተብሎ ነው ወደ ስራ የተገባው።

በዓለም ላይ ድርቅ፣ የመሬት መራቆትና በረሃማነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየቀኑ የምንሰማው መረጃ ሆኗል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚሄደው የህዝብ ቁጥርና ከፍላጎት የተነሳ፣ ጤናማ የመሬት ሽፋን እየቀነሰ እንዲሄድ እና የተፈጥሮ ሐብቱ እንዲመናመን በማድረግ ድርቅ፣ ጎርፍና ሰደድ እሳት በተደጋጋሚ በዓለማችን የተለያዩ ጫፎች እንዲከሰት አድርጓል።

ታዲያ በየዓመቱ የዓለም በረሃማነት እና ድርቅን የመከላከል ቀን በመሬት ላይ እየቀነሰ ስላለው የደን ሽፋን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ይህን አንገብጋቢ ችግር ለመቅረፍ ህዝቦች በጋራ እንዲሰሩ ለማበረታታት የሚከበር ነው።

እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የዓለም መሪዎች በሪዮ ምድር ጉባኤ ላይ በረሃማነት፣ የብዝሃ ሕይወት መጥፋት እና የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ ችግሮችን ለመፍታት ተሰብስበው ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በረሃማነትን ለመዋጋትም በ1994 (UNCCD) ተመሰረተ።

በዚህ አላበቃም እ.ኤ.አ. በ 2007 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ 2010 እስከ 2020 አስር ዓመታት በረሃ እና በረሃማነትን ለመዋጋት አወጀ።

ይህ ተነሳሽነት መሬትን የመንከባከብ አስፈላጊነትን ለማስገንዘብ እና በረሃማነትን እና ድርቅን ለመከላከል የጋራ እርምጃዎችን ለማበረታታት ያለመ ነበር።

ይህ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት መንግስታትን፣ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን በጋራ በመሆን አካባቢን ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት እና የመሬት ሐብትን በብቃት ለማስተዳደር እንዲሰሩ ያደርጋል ተብሎ ነው ወደ ስራ የተገባው።

እያደገ የመጣው የዓለም የህዝብ ቁጥር ዘላቂነት ከሌለው የምርት እና የፍጆታ ዘይቤ ጋር ተዳምሮ የተፈጥሮ ሐብት ፍላጎትን በማቀጣጠል በመሬት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር እስከ መራቆት ይደርሳል።

በረሃማነት እና ድርቅ በየዓመቱ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመፈናቀል አደጋ ላይ ጥሏል።

በዓለም ላይ ካሉት 8 ቢሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች  ሲሆኑ እነዚህም በታዳጊ ሀገራት ላይ ይገኛሉ፤ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ በመሬት እና በተፈጥሮ ሐብት ላይ በቀጥታ ጥገኛ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ።

በረሃማነትን እና ድርቅን ለመከላከል በሚል በየዓመቱ ሰኔ 10 የሚከበረው የበረሃማነት እና የድርቅ ቀን የዘንድሮ መሪ ቃል  “ውርሳችንም ተስፍችንም ለሆነችው ምድር በአንድ ላይ እንቁም” የሚል ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በረሃማነትና ድርቅን ለመከላከል በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን እየተከለች ትገኛለች።

በዘንድሮውም ዓመት በሚከናወነው የአረንጓዴ  አሻራ መርሐ-ግብር አካባቢያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ዝግጅት እየተካሄደ ይገኛል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መረጋጋት፣ ሰላም እና ዕድገትን ለማረጋገጥ በጣም ውድ ሐብታችን መሬትን ከበረሃማነት መከላከል የሁላችንም ድርሻ ነው።

በናርዶስ አዳነ

 


Feedback
Top