ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - አቶ አደም ፋራህ

4 Mons Ago 1008
ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - አቶ አደም ፋራህ

ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።

የብልጽግና ፓርቲ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መድረኩ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና የተረጂነት አመለካከትና ተግባርን ከመቀነስ አንጻር በተሰሩት ስራዎች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።

በውይይቱም ፓርቲው እና መንግስት በሱፐርቪዢን ምልከታ እና በሌሎችም ጊዜያት ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

ለአብነትም የምርት አቅርቦትን ከማሻሻል፣ የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተረጂነት አመለካከት ተግባርን ለመቀነስ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የመስራት አቅም ያላቸው ዜጎች ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ለማድረግ መሰራት አለበት ሲሉ ገልፀዋል።

የምግብ ዋስትናን እና የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ መቻል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ አቅም መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተረጂነት አመለካከቶችን በማስወገድ ሰርቶ የመለወጥ ራዕይ ያለውንና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባም ገልፀዋል።

በዚህም የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ምርት መግባታቸውን ጠቁመው የምርት አቅርቦት እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የታዩ ጉድለቶችን በመፍታት ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ አምራችን ከሸማቾች ጋር ለማገናኘት በተሰሩ ስራዎችም በረከት ያሉ የገበያ ማዕከላት ተቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተወሰዱት የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎችም ውጤት ማስገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ህገ-ወጥ ደላሎችንና ኬላዎችን ከመቆጣጠር እና ከማስወገድ አንጻርም አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ የሱፐርቪዥን ስራዎች ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ያመላከተ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮችም የተለዩበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያ ካሚል በበኩላቸው፤ ከስራ ዕድል ፈጠራ በበጀት ዓመቱ የተያዘለውን ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ ኢኒሼቲቮችን የስራ ዕድል መፍጠሪያ በማድረግ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ ባቀረቡት ጽሁፍ የተረጂነት አመለካከቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሰርቶ መለወጥ የሚችል ዜጋ ለመፍጠር አመለካከት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የፓርቲና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


Feedback
Top