ለሕሊና (ለሞራል) ጉዳት ካሳ 1 ሺህ ብር ይበቃል?

9 Mons Ago 1534
ለሕሊና (ለሞራል) ጉዳት ካሳ 1 ሺህ ብር ይበቃል?

ለሕሊና (ለሞራል) ጉዳት ካሳ 1 ሺህ ብር ይበቃል?

ሕጉ ምን ይላል?

እነዚህን ሁለት በሀገራችን የመጨረሻ የዳኝነት አካል እስከሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ የጉዳት ካሳ ክርክሮችን በአጭሩ  አስነብባችሁና የራሳችሁን ዳኝነት ከሰጣችሁ በኋላ ሰበር የሰጠውን ውሳኔ በአጭሩ እናያለን።

 የልጅ ሞትና የሕሊና ጉዳት

ወ/ሮ ዘሀራ አባኑር እና አቶ  መሀመድ አባአሊ ልጃቸው በደረሰበት የመኪና አደጋ በመሞቱ የመድሕን ሽፋን ሰጥቶ ከነበረው የኢንሹራስ ኩባንያ ጋር ተከራከሩ፡፡

ልጃቸውን በአደጋው ምክንያት በማጣታቸው የቀረባቸው የገንዘብ ጥቅም ብር 52 ሺህ ሕሊናቸው ላይ ለደረሰው ጉዳት ደግሞ ብር 2 ሺህ እንዲከፈላቸው የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ይግባኝ የተጠየቀበት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰኑ፡፡

ይሄ ውሳኔ የተሰጠበት የኢንሹራንሱ ኩባንያ ቅር በመሰኘቱ የሕሊና ጉዳት (የሞራል ጉዳት) ካሳ ከ1 ሺህ ብር እንደማይበልጥ በሕግ ተደንግጓልና በሕግ ከተደነገገው የገንዘብ መጠን በላይ የሕሊና ጉዳት ካሳ እንድከፍል በመወሰኑ የተፈፀመው የሕግ ስሕተት ይታረምልኝ ሲል አመለከተ፡፡

 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ሕጉን ተርጉሞ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በቅድሚያ እናንተ ሕሊናችሁን ብቻ በመጠቀም ዳኙ  ብትባሉ ኖሮ ወ/ሮ  ዘሀራና አቶ መሀመድ ልጃቸውን በማጣታቸው ሕሊናቸው ወይም መንፈሳቸውና ቅስማቸው ላይ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ይገባቸዋል?

የሕሊና ጉዳት በገንዘብ ሊካስ ይችላል? ከተቻለ በምን ያህል?

ባይወልዱትም ያሳደጉትን ልጅ ማጣት

ኒሻን አለማየሁ የእህቷን ልጅ ወንድማገኝ ይልማን አንደ ልጇ አድርጋ እያሳደገች ትኖር ነበር ፡፡

ከእህቷ ልጅ ጋር የምትኖረው የምትሰራበት የመንግስት የእርሻ ልማት በሰጣት ቤት ውስጥ ሲሆን፤ ወንድማገኝ የሚኖርበት ግቢ ሲቦርቅ ያደገበት ቢሆንም አንድ ቀን ግን በመጫወት ላይ እያለ በግቢው የተዘረጋው ኤሌትሪክ ይዞት ሞተ፤ 14 ዓመቱ ነበር፡፡

አሳዳጊ  አክስቱ በድርጅቱ የሕብረት ስምምነትና በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት የጉዳት ካሳ ይከፈለኝ ስትል በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ፍርድ ቤት  የእርሻ ልማት ድርጅቱን ከሰሰች።

ፍርድቤቱም መስከረም 3 ቀን 1999 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ (የሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 5 ገፅ 153 ላይ) የገንዘቡን መጠን ባይጠቅስም ካሳ እንዲከፈላት ወሰነ፡፡

የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ውሳኔውን አፀናው፡፡

የእርሻ ልማት ድርጅቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረበው ክርክር በድርጅቱ ሠራተኞች የሕብረት ስምምነት መሠረት፤ ሕፃን ወንድማገኝ የወ/ሮ ኒሻን የወለደችው ልጅ ወይም በጉዲፈቻ የምታሳድገው ባለመሆኑ ድርጅቱ በሕብረት ስምምነቱ መሠረት ኃላፊነት የለበትም የሚለውን አስወሰነ፡፡

በፍትሃብሔር ሕጉ መሰረት ደግሞ ሕፃን ወንድማገኝ ለሞት የተዳረገው የድርጅቱ ንብረት በሆነው የኤሌትሪክ መስመር በመሆኑ ድርጅቱ ኃላፊነት አለበት አለ።

ሰበር ወ/ሮ ኒሻን ሕፃን ወንድማገኝ በመሞቱ ምክንያት የሚቀርባት ቀለብ ወይም የምግብና የልብስ መሰረታዊ የመተዳደሪያ ገቢ ስለሌለ የገንዘብ ጥቅምን በተመለከተ ካሳ አይገባትም ብሎ ደመደመ፡፡

ሆኖም  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  ወ/ሮ ኒሻን ተንከባክባ ያሳደገችው ልጅ በአደጋው ምክንያት በመሞቱ የሕሊና ጉዳት ደርሶባታል ስለዚህ ሕሊናዋ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ ይገባታል አለ፡፡

ስንት የሚለውን በቅድሚያ እናንተ ወስኑና በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ውስጥ ግምታችሁን ላኩልን።

ሰበር ምን አለ?

የአቶ መሀመድ እና የወ/ሮ ዘሀራ ልጅ ላይ ለደረሰው የሕሊና ጉዳት በሰበር መዝገብ ቁ. 6942 የካቲት 26 2014 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2116(3) ላይ የሕሊና ጉዳት ካሳ ከ1 ሺህ ብር ሊበልጥ ስለማይችል 2 ሺህ ብር መወሰኑ አላግባብ ነው በማለት፤ ለልጃቸው ሞት ለሁለቱ ወላጆች የ1 ሺህ ብር የሕሊና ጉዳት ካሳ ብቻ እንዲከፈላቸው ወሰነ፡፡

የወ/ሮ ኒሻንን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ የአፋር ክልል ፍርድቤቶችን ውሳኔ በማሻሻል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ.መ.ቁ 3109 ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ሌላ ተጨማሪ ካሳ አይገባትም፤ ሕሊናዋ ላይ ለደረው ጉዳት ግን 1 ሺህ ብር ይበቃታል ሲል ወሰነ፡፡

ስለ ሕሊና ጉዳት ካሳ ሕጉ ምን ይላል?

አንድ ሰውን በሌላው ሰው ስህተት፣ ስራ፣ ጥፋት፣ወይም ንብረት በሞት ስናጣው ወይም አካል ጉዳት ሲደርስበት ለጉዳቱ ተጠያቂ የሚሆን ሰው ይኖራል፡፡

የምናጣው ቁሳዊ ወይም የገንዘብ ጥቅምም እንደየሁኔታው ይካሳል፡፡ ማስላት አስቸጋሪ ከሆነም በሕጉ መሰረት ዳኞች በሕሊናቸው ግምት የሚገባንን ካሳ ይወስናሉ፡፡

ከቁሳዊ ጉዳት ውጭ ግን ሕሊናችን ላይ የሚደርስ ጉዳት አለ። በርግጥ ጉዳቱ በገንዘብ ሊፋቅ ሊካካስ አይችል ይሆናል ይህ ግን አያስፈልግም ማለት አይደለም።ሕሊናችንንም ለመካስ መሞከር አለበት፡፡

በ1952 ዓ.ም የወጣው የ64 ዓመቱ የፍትሐ ብሔር ሕጋችን በአንቀፅ 2116(3) ላይ በማንኛውም ሁኔታ ሕሊናችን ላይ የሚደርስ ጉዳት ካሳው ከ 1,000 (አንድ ሺህ) ብር እንደማይበልጥ ይደነግጋል።

ከ64 ዓመት በፊት 1ሺህ ብር ብዙ ነገር ሊያደርግ ይችል ይሆናል፡፡ የዛሬን አንድ ሺህ ብር ግን እናውቀዋለን።

የመጨረሻው ሕግ የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን 1ሺህ ብርን አሁን ካለው ዋጋ ከያኔውና ከአሁኑ የኑሮ ውድነት አንፃር ሕጉን ተርጉሞ የሕሊና ጉዳት ካሳ መጠንን ሊያሻሽለው አልቻለም።

ሕሊናችን ላይ የሚደርስ ጉዳት ምን ያህል ቢከብድ በ1ሺህ ብር እንደተገደበ ለ64 ዓመት ዘልቋል፡፡

የሕሊና ጉዳት የሚያስከትለው የመንፈስ ስብራት በምንወደው የቅርብ ቤተሰብ ልጅ ፣አባት፣ እናት፣ ወንድም ወይም እህት ሞት ሲደርስብን ምንም አይነት የገንዘብ ጥቅም ያጣነውን ሰው ስለማይተካልን እጦቱ ከባድ ነው፡፡

እንደ ማፅናኛ ወይንም በጥፋቱ ወይም በስህተቱ መፀፀቱን እንደመግለጫ ከጉዳት አድራሹ በሕግ የምናገኘው ካሳ ግን 1 ሺህ ብር ብቻ ወይም ከዚያ በታች ነው፡፡

እስቲ ይህን ጥያቄ እናንሳ፤ የሕሊና ጉዳት (የሞራል ጉዳት) ካሳ እውን ሕጋችን እንደሚለው በዚህ ዘመን ላይ የ1 ሺህ ብር ካሳ ይበቃዋል? እስቲ ሀሳብ ስጡበትና እንወያይበት።

 


Feedback
Top