የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለሀገር ውስጥ ባንኮች ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?

19 Hrs Ago 113
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለሀገር ውስጥ ባንኮች ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት በቴክኖሎጂ የላቀና ዘመናዊ አሰራር የሚያመጣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባንኮችን የሚያጠናክር ነው ሲሉ የብሔራዊ ባንክ የባንኮች ሱፐርቭዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ተናግረዋል፡፡
 
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚፈቅደው አዋጅ፣ የተለያዩ መስፈርቶችንና ድንጋጌዎችን ያካተተ እና የሀገር ውስጥ ባንኮችን በማይጎዳ መልኩ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት ጥብቅ የአሰራር ሥርዓት የተዘረጋበት ነው ብለዋል፡፡
 
ባንኮቹ ወደ ሀገር ሲገቡ በቅድመ ፈቃድ፣ በድህረ ፈቃድ እና በፈቃድ ጊዜ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ሰነዶችና ታሪካቸው ተፈትሾ የሚገቡበት አግባብ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑንም አቶ ፍሬዘር ለኢቲቪ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ መሰናዶ ገልጸዋል፡፡
 
የውጭ ባንኮቹ የሚሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተገደቡ በመሆናቸው የሀገር ውስጥ ባንኮችን አይጎዱም ነው ያሉት፡፡
 
ባንኮቹ ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ ሲገቡም የሀገር ውስጥ ባንኮች ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን በመፈተሽና የተወዳዳሪነት መንፈስን በመፍጠር የበለጠ ተደራሽነታቸውን እንዲያሰፉ ያደርጋል ነው ያሉት አቶ ፍሬዘር፡፡
 
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው የባንክ የሥራ ዘርፉ ከ30 ዓመት በላይ ለውጭ ባለሐብቶች ዝግ ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች በራሳቸው እግር ጠንክረው መቆም ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድጉ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ለውድድሩ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ገልጸው፤ አንዳንድ ባንኮችም ራሳቸውን በማዋሃድ ጠንካራ አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
 
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ባንኮች የሚያጋጥማቸውን ውድድር ለመቋቋም በአዋጁ የተወሰነውን ድርሻ በመሸጥ እድገታቸውን ሊያፋጥኑ እንደሚችሉም አቶ ዘመዴነህ ጠቁመዋል፡፡
 
በመሀመድ ፊጣሞ

Feedback
Top