ከአሸናፊነትም ከወርቅ ሜዳልያም በላይ የገዘፈ፣ ሀገር ማለት ምን እንደሆነ በተግባር የተገለጠበት፣ ምን አልባትም ሊደገም የማይችል፣ ከአዕምሮ በላይ የሆነ የአንድ አፍሪካዊ አትሌት ገድል ነው፡፡ “ሀገሬ የላከችኝ እንዳቋርጥ አይደለም” ጆን ስቴፋን አክዋሪ
ለአንድ አትሌት ሀገርን በኦሎምፒክ መድረክ መወከል ከፍ ሲል ደግሞ አሸናፊ መሆን ትልቁ ግብ ነው፡፡ ይህንን ያደረጉ ዕልፍ ናቸው፡፡ ይሄኛው ታሪክ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ማሸነፍ ቀርቶ መጨረሻ ለመውጣት እንኳን በርካታ ሰዓት የወሰደበት፣ ነገር ግን ኦሎምፒክ ሲታወስ ሁሌም ስሙ ከአሸናፊዎች በላይ ገዝፎ የሚነሳ ሰው ታሪክ ነው፡፡

ጊዜው 1968 ሜክሲኮ ኦሎምፒክ ሲሆን ታሪኩ የሚጀምረውም እዚህ ጋር ነው፡፡ በመድረኩ በማራቶን 78 አትሌቶች ለአሸናፊነት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ በግብርና ሙያ ከሚተዳደሩ ቤተሰቦቹ የተገኘው እና ታንዜንያን የወከለው ጆን ስቴፋን አክዋሪ ነው፡፡ ከ42 ኪሎ ሜትር ዘለግ የሚለው ውድድር ተጀመረ፡፡ አክዋሪ እስከ 19 ኪሎ ሜትር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ዘለቀ፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ ግን ታጅበው ከሚሮጡት አትሌቶች ውስጥ የሚገኘው አክዋሪ ተደነቃቅፎ በመውደቁ እግሩ እና እጁ ክፉኛ ተጎዳ፡፡ ብዙዎቹ አትሌቶች በወደቁበት የህክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸው ወድድሩን በዚያው ሲያቋርጡ ስቴፋን ኦኩዋሪ ግን አይደለም ለመሮጥ ለመንቀሳቀስ እንኳን ፈታኝ ከነበረው ህመሙ ጋር እየታገለ መሮጡን ቀጠለ፡፡
ከባህር ጠለል በላይ 2200 ከፍታ ባለው ቦታ እና እጅግ ፈታኝ በሆነው የአየር ጸባይ ምክንያት ብዙዎች በኦክስጅን ታግዘው ከውድድሩ ሲሰናበቱ እሱ ግን ደም እየፈሰሰው እግር እና እጁን በፋሻ ታስሮ በዝግታ መሮጡን ቀጥሏል፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ጉዳቱ እንዳይባባስ እንዲያቋርጥ በተደጋጋሚ ቢነግሩትም እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ሁነቱን ስቴዲየም ውስጥ ሆነው በቴሌቪዥን የሚከታተሉ ተመልካቾች ለአሸናፊነት ከሚደረገው ትንቅንቅ በላይ ይሔኛው ትኩረታቸውን ስቦታል፡፡

በዚህ መሀል አሸናፊው ታወቀ፡፡ ኢትዮጵያዊው አትሌት ማሞ ወልዴ አድካሚውን ውድድር በበላይነት አጠናቀቀ፡፡ በአትሌት አበበ ቢቂላ በ1960 ሮም ኦሎምፒክ የተጀመረው የባዶ እግር የማራቶን ድል ለ3ኛ ተከታታይ ጊዜ በአትሌት ማሞ ወልዴ ሀትሪክ የተሰራበት ሆነ፡፡ በመድረኩ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ባለ ድሉ አበበ ቢቂላ ቢያቋርጥም ማሞ ወልዴ ኢትዮጵያ ሌላ አዲስ ጀግና እንዳላት ለአለም ያሳየችበትም ሆነ፡፡
ከባድ ጉዳት ያጋጠመው ስቴፋን አክዋሪ ግን የቱንም ያክል ከአሸናፊዎቹ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ቢሆንም እጅ አልሰጠም። ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡት አትሌቶች ሜዳልያቸውን ለመቀበል ወደ ፖዲየም አመሩ፡፡ ሽልማቱ እየተበረከተላቸው እያለ በስቴዲየም የሚገኝው ተመልካች ሩጫውን ያላጠናቀቀ አትሌት አለ ሽልማቱ መዘግየት አለበት በማለት ስሙን እየጠሩ መጮሀቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከሽልማት ስነ ስርአቱ በኋላ መምሸቱን ተከትሎ ሁሉም ሰው ሲበተን አዘጋጆቹ እና የተወሰኑ ተመልካቾች ብቻ የስቴፋን አክዋሪ መጨረሻ ለማየት በስቴዲየም ተቀምጠዋል፡፡ በወደቀበት ሰአት ጉልበቱ ቦታውን የለቀቀው እና ስብራት ያጋጠመው አትሌት ህመሙን፣ ስቃዩን እና ሀገሩ ታንዜንያን ተሸክሞ እየወደቀም እየተነሳም አሸናፊው ማሞ ወልዴ ከገባበት አንድ ሰአት ዘግይቶ ስቴዲየም ደረሰ፡፡ በዚያ ያሉ ተመልካቾች በደስታ ጮቤ ረገጡ፡፡ ያላቸውንም ክብር ገለጹለት፡፡

23 ኪሎ ሜትሮችን ከከባድ ህመም ጋር የታገለው ሰው በጽናት 57ኛ በመሆን የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቀቀ፡፡ ስቴፋን አክዋሪ 21 አትሌቶች በጉዳትም በድካምም ውድድሩን ማጠናቀቅ ባልቻሉበት የሜክሲኮ ኦሎምፒክ 3 ሰአት ከ25 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ርቀቱን ለማጠናቀቀ የወሰደበት ሰአት ሆኖም በክብር ተመዝግቧል፡፡ በነገሩ ሁሉ የተገረሙ ጋዜጠኞች ጠየቁት “ሀገሬ የላከችን እንድጀምር ሳይሆን እንዳጠናቅቅ ነው” በማለት መለሰላቸው፡፡ ያጋጠመውን ሁሉ የተመለከተው አንድ የ9 አመት ልጅ ከወላጆቹ ጋር ሆኖ አድናቆቱን ገለጸለት፡፡ በአንድ ወቅት ወደ ታንዜንያ አምርቶም እንደሚጎበኝው ቃል ገባለት፡፡ ከአመታት በኋላም የያኔው ልጅ ቃሉን መፈጸሙን ስቴፋን አክዋሪ ተናግሯል፡፡

ሩጫ ካቆመ በኋላ ወደ ግብርናው የተመለሰው ጽኑ ሰው በ2000 ሲድኒ ኦሎምፒክ የማራቶን አሸናፊዎችን እንዲሸለም ተጋብዞ ወደ አውስትራሊያ ሲያመራ የወቅቱን ሻምፒዮን ገዛህኝ አበራን የወርቅ ሜዳልያ ያጠለቀለት እሱ ነው፡፡
የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ አራት የወርቅ ሜዳልያ ባመጡበት የ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ የክብር አምባሳደር አድርጎ እውቅና ሲሰጠው ሀገሩም የምንጊዜም ጀግና ብላ የክብር ኒሻን ሸልማዋለች፡፡
ጥንካሬን እና ተስፋን ከግብርናው የወሰደው፣ የኦሎምፒክን ትርጉም የገለጠው እና የአፍሪካውያን የጽናት ተምሳሌት መሆኑን በተግባር ያሳየው ጆን ስቴፋን አክዋሪ አሁን 83ኛ አመቱ ላይ ይገኛል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ