በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ንጉሱ በቀጥታ ካልፈቀዱ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን እንደማይችል ታሪክ ያስረዳናል።
የደርግ ዘመነ መንግስትም የውጭ ዜጎች የመሬትና የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዳይዙ በሕግ ከልክሏል። በኋላ በኢንቨስትመንት አዋጅ 1180/2012 እና ይህንኑ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ መሰረት በተወሰነ መልኩ ላላ የማለት አዝማሚያ ታይቷል።
በተለይም ደንቡ 10 ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ኢንቨስት ላደረጉ የውጭ ዜጎች አንድ መኖሪያ ቤት ብቻ የሚፈቀድበት አግባብ ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡
በእንደራሴዎች ምክር ቤት የረቂቁን አስፈላጊነት ያብራሩት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ ረቂቁ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው ነበር።
ለመሆኑ ረቀቁ ከሕግ አግባብ እንዴት ይታያል? ከነባራዊው ሁኔታው ጋር እንዴት ተጣጥሞ ይተገበራል? ውሳኔውስ በኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት አበርክቶ ይኖረዋል? ሲል የኢቲቪ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ ጠይቋል።
አዋጁን ካረቀቁት መካከል የሆኑት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ማርቀቅ አስተባባሪ አቶ ጠገነኝ ትርፌ፤ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን ከዜጎቻቸው እኩል የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋታቸውን አንስተዋል
በኢትዮጵያም የዜጎችን ተጠቃሚነት በማያጣብብ መልኩ ለውጭ ሀገር ዜጎች መፍቀድ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
ገደቦች ተቀምጠው የውጭ ሀገር ዜጎች ለመኖሪያ ቤት ዓላማ ብቻ የሚውል መሬት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅድ ሕግ ለመዘርጋት መታቀዱን ይገልጻሉ።
የኢኮኖሚ ከፍተኛ ተመራማሪው አቡሌ መሐሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ መፍቀድ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
“ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከፍተኛ የስራ ዕድልን ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል”ይላሉ።
ይሁንና የኢኮኖሚ ገበያውን በማይረብሽና የዜጎችን የመሬት አጠቃቀም በማያጣብ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሰብለ አሰፋ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የሪል ስቴት ልማት እምብዛም ውድድር የሌለውና መካከለኛ ገቢ ያለው ኢትዮጵያዊ እንኳን ሊገዛው የማይችል ዋጋ የሚቀርብበት በመሆኑ የውጭ ኢንቨስትሮችን ለማሳተፍ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የውጭ ዜጎች በዚህ ልክ መብት ሲያገኙ ገደቦች ሊኖሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ናይጀሪያ ተመሳሳይ ሃብቶችን ለውጭ ዜጋ ክፍት ያደረጉበትን መንገድ በመቃኘትና ልምድ በመውሰድ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስቀረት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
በተለይ ቦታዎች በከፍተኛ መጠን በውጭ ሀገራት ተይዘው ዜጎች በሀገራቸው መሬት ባዳ እንዳይሆኑ እንዲሁም የመንግስትም ፖሊሲ ላይ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የፕራግማ ካፒታል ስራ አስፈጻሚ መርዕድ ብስራት ፍቀረዮሐንስ በበኩላቸው፤ “ሀገር ውስጥ ያለው የቤት አቅርቦት ለኢትዮጵያውያን እንኳን ያልበቃ በመሆኑ ረቂቁ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አይደለም” ብለዋል።
በመሆኑም አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
"በተለይም በከተሞች ያለው የመሬት አቅርቦት ለኢትዮጵያውያን ቤት ባለቤት እንዲሆኑ በሚረዳ መልኩ በፖሊሲ ማዕቀፍ ደረጃ ሊሰራበት ይገባል" ይላሉ።
ከአዋጁ ትግበራ አስቀድሞ ባንኮቻችን የሞርጌጅ ገበያዎች ላይ እንዲሰሩ ለማድረግ የሞርጌጅ ሪፋይናንሲንግ ድርጅት ተቋቁሞ በዚያ በኩል የፋይናንስ ሥርዓቱን በጋራ ማጤን እንደሚገባ አመላክተዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#EBC #EBCdotstream #የንብረት_ባለቤትነት #ረቂቅ_አዋጅ