ትላልቅ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በላቀ ድምቀት እና በስኬት ለመወጣት፣ የተናጠል ተቋማዊ ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ተቋማት እና ግብረ ኃይሎች ተናብቦ እና ተቀናጅቶ መሥራት ወሳኝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ32ኛው የተመድ አየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴን በመሰብሰብ የሰጡት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በብቃት ለማስተናገድ የያዘችውን የላቀ ዝግጁነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ከ80 ሺህ የዓለም መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎች እና ባለሀብቶች የሚታደሙበት ግዙፍ መድረክ ነው።
እንዲህ ዓይነቱን ታሪካዊ ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ የፀጥታ፣ የመሠረተ ልማት፣ የትራንስፖርት፣ የመስተንግዶ፣ የቴክኖሎጂ እና የዲፕሎማሲ ሥራዎች እንደ አንድ ሰንሰለት ተሳስረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ሁሉም ግብረ ኃይሎች ተናብበው እንዲሠሩ በአጽንኦት አሳስበዋል።
ተናብቦ መሥራቱ በየዘርፉ ያሉ አካላት የሥራ መደራረብን በማስቀረት ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ግብ በተመሳሳይ ጥራት እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል።
ይህም ዝግጅቶችን አስቀድሞ በመፈተሽ እና በመገምገም የሚታዩ ክፍተቶችን በወቅቱ ለማረም እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።
የ32ኛው የአየር ንበረት ጉባኤ (COP32) ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሥራዎች በከፍተኛ አመራር ደረጃ መገምገማቸው፣ ኢትዮጵያ ያላትን የተቋማዊ ቅንጅት ልምድ ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ጉባኤውን የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ ታሪካዊ አጋጣሚ ለማድረግ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያመላክታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ኢትዮጵያ ለታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች የቆመችለትን ሁሉን አቀፍ የመንግሥት አካሄድ በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: